28 አገራት እርዳታ በሚሹ የጋዛ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመ 'ኢሰብዓዊ ግድያ' እስራኤልን አወገዙ

ከተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማከፋፈያ ጣብያዎች ዱቄት ተቀብለው የተሸከሙ ፍልስጤማውያን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች 27 አገራት በጋዛ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቅርበው፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ስቃይ "ከዚህ በፊት ከነበረው ሁሉ የከፋ" ሆኗል አሉ።

በዚህ የጋራ መግለጫ የእስራኤል የእርዳታ አሰጣጥ መንገድ አደገኛ ነው ሲል የኮነኑ ሲሆን፣ ምግብ እና ውሃ ፍለጋ ለሚመጡ "ጠብታ እርዳታን መስጠት እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ኢሰብአዊ ግድያ" አውግዘዋል።

በጋዛ ሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያን እርዳታ ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ እያሉ ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን እና ሌሎች 19 ሰዎች ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ መሞታቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገራቱን መግለጫ "ከእውነታው የራቀ እና የተሳሳተ መልዕክት ለሐማስ የሚያስተላልፍ" ሲል ውድቅ አድርጎታል።

ሚኒስቴሩ የታጠቀው ቡድን አዲስ የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን መልቀቅ ላይ ከመስማማት ይልቅ ውሸትን በማሰራጨት እና የእርዳታ ስርጭትን በማዳከም ከስሷል።

እስራኤል ከሐማስ ጋር እያካሄደች ባለችው ጦርነት ላለፉት 21 ወራት በጋዛ ላይ የወሰደውን እርምጃ የሚያወግዙ ብዙ ዓለም አቀፍ መግለጫዎች አሉ።ይህ መግለጫ ግን ከሌሎቹ በተለየ ግልጽ ሆኖ የቀረበ ነው።

የመግለጫው ፈራሚዎች አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ኒውዚላንድ እና ስዊዘርላንድን ጨምሮ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና 27 አገራት ናቸው።

መግለጫው የሚጀምረው "በጋዛ ያለው ጦርነት አሁኑኑ ማብቃት አለበት" በማለት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመቀጠልም "በጋዛ ውስጥ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ስቃይ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። የእስራኤል መንግሥት የእርዳታ አሰጣጥ መንገድ አደገኛ ነው። አለመረጋጋትን ያባብሳል እንዲሁም የጋዛውያንን ሰብዓዊ ክብር ያሳጣል።

"እፍኝ የምግብ እርዳታ መስጠትን እና ሕጻናትን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ኢሰብዓዊ ግድያ እናወግዛለን። ከ800 የሚበልጡ ፍልስጤማውያን እርዳታ ሊቀበሉ ሲሉ መገደላቸው አሰቃቂ ነው" ይላል።

ከመግለቻው በኋላ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት እንዳስረዱት በጋዛ ውስጥ "የተጨነቁ እና የተራቡ ሕፃናትን" የገደሉ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ጨምሮ "ማብቂያ የሌለው ስቃይ" እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት ለጋዛ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ፓውንድ ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ይፋ ያደረጉት ላሚ "የእስራኤልን ደህንነት እና የመኖር መብቷ ጽኑ ደጋፊ ነን" ቢሉም የመንግሥት እርምጃ ግን "እስራኤል በዓለም ፊት ያላት ቁመና ላይ ያልተነገረ ጉዳት እያደረሰ እና የእስራኤልን የረዥም ጊዜ ደኅንነት የሚጎዳ ነው" ብለዋል።

ከግንቦት ወር ጀምሮ እርዳታ የሚጠብቁ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች በየቀኑ ይወጣሉ።

እስራኤል ለ11 ሳምንታት ወደ ጋዛ ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳይገባ አግዳ ከቆየች በኋላ የተባበሩት መንግሥታትን ገሸሽ በማድረግ እና ከአሜሪካ ጋር በመሆን የጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽንን አቋቁማ እርዳታ በማከፋፈል ላይ ትገኛለች።

የጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን እስራኤል በጋዛ በመሠረተቻቸው ወታደራዊ ቀጠናዎች፣ በአሜሪካ የግል የደህንነት ጠባቂዎች በመታገዝ የሚያከፋፍለው የምግብ እርዳታ በሐማስ እንዳይሰረቅ ይከላከላል ትላለች።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አጋሮቹ የእርዳታ አሰጣጥ ስርዓቱ ደህንነቱ ያልተጠበቀ እና የገለልተኝነት፣የአለማዳላት እና የነጻነት ሰብዓዊ መርሆችን የሚጥስ ነው በማለት ለመተባበር ፈቃደኛ አልሆኑም።

ባለፈው ማክሰኞ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት፣ ፋውንዴሽኑ መንቀሳቀስ ከጀመረባቸው ካለፉት ስምንት ሳምንታት ወዲህ በእርዳታ ጣቢያዎቹ አካባቢ 674 ግድያዎች መፈጸማቸውን መመዝገቡን ገልጿል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች የእርዳታ አቅራቢዎች አካባቢ ደግሞ 201 ግድያዎች ተመዝግበዋል ሲል አክሏል።

ቅዳሜ እለት፣ ሌሎች 39 ሰዎች በካን ዮኒስ እና በአቅራቢያው ራፋህ በሚገኙ ሁለት የፋውንዴሽኑ የእርዳታ መስጫ ጣቢያዎች አቅራቢያ ተገድለዋል ሲል የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር ጣቢያዎቹ ከመከፈታቸው በፊት "ተጠርጣሪዎች" ወደ እነርሱ እንዳይቀርቡ ለመከላከል ወታደሮቹ የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሳቸውን ገልጿል።

እሁድ ዕለት እንዲሁ በሰሜን ጋዛ አቅራቢያ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ መኪናዎች የሚሄዱ 67 ሰዎች መገደላቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የእስራኤል ጦር ወታደሮች "የተጋረጠን አሁናዊ ስጋትን ለማስወገድ" የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሳቸውን ገልጾ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር አስተባብሏል።

ይህንን ድርጊት ተከትሎ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የጋዛ ረሃብ ቀውስ "አዲስ የተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ደርሷል" ሲል አስጠንቅቋል።

እናት የሞተ ልጇን አቅፋ ስታለቅስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በደቡብ ጋዛ የሚገኘው የናስር ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች የአላ አል ናጃር የሦስት ወር ሕፃን ልጅ ዬያ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል

"ሰዎች በሰብዓዊ ዕርዳታ እጦት እየሞቱ ነው። 90,000 ሴቶች እና ሕጻናት በምግብ እጥረት በመጎዳታቸው አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል" ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

በጋዛ ሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት እንደተናገረው ከቅዳሜ ጀምሮ 19 ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት መሞታቸውን እና በሚቀጥሉት ቀናት "ብዙ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ" ሲል አስጠንቅቋል።

በዴር አል ባላህ የሚገኘው የአል አቅሳ ሆስፒታል ቃል አቀባይ ዶክተር ካሊል አል ዳክራን "ሆስፒታሎች ለታካሚዎች ወይም ለሠራተኞች ከእንግዲህ ወዲያ ምግብ ማቅረብ አይችሉም፤ አብዛኛዎቹ በከፍተኛ ረሃብ ምክንያት ሥራቸውን መቀጠል አልቻሉም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ሆስፒታሎች በረሃብ ለሚሰቃዩ ሕፃናት አንድ ጠርሙስ ወተት መስጠት አይችሉም። ምክንያቱም ሁሉም የሕፃናት የዱቄት ወተት ከገበያ ጠፍቷል" ብለዋል።

በምግብ እጥረት የተነሳ ገበያዎች መዘጋታቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

"ልጆቼ ሌሊቱን ሙሉ በረሃብ ምክንያት ያለቅሳሉ። ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ አንድ ትንሽ ሳህን ምስር ብቻ ነበራቸው።ዳቦ የለም፣አንድ ኪሎ ዱቄት ከሳምንት በፊት 80 ዶላር ነበር የሚሸጠው" ሲል የሁለት ልጆች አባት የሆነው ፀጉር አስተካካዩ መሀመድ ኢማድ አልዲን ለቢቢሲ ተናግሯል።

በተጨማሪም የ27ቱ አገራት መግለጫ እስራኤል 2.1 ሚሊዮን የጋዛን ሕዝብ በደቡባዊ ራፋህ "የሰብዓዊነት ከተማ" ስትል ወደጠራችው አካባቢ ለማዘዋወር ያቀረበችውን ሀሳብ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾ "አስገድዶ በቋሚነት ማፈናቀል የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን መጣስ ነው" ብለዋል።

እስራኤል፣ ሐማስ እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "ይህን አስከፊ ግጭት በአስቸኳይ፣ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲያስቆሙት" አሳስበዋል።

አክለውም "አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲረግ፣ለደህንነት እና ሠላም ፖለቲካዊ አማራጮችን ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን" አስታውቀዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦረን ማርሞርስቴይን ትችቱን ውድቅ አድርገውታል።

"ሁሉም መግለጫዎች እና ሁሉም ውንጀላዎችታጋቾችን ለመልቀቅ እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ላለመድረስ ተጠያቂ ወደ ሆነው ብቸኛው አካል፣ ይህንን ጦርነት ወደ ጀመረው እና ወዳራዘመው ሐማስ ማነጣጠር አለባቸው" ብለዋል ።

"ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነትን ከማድረግ ይልቅ በእስራኤል ላይ ውሸትን ለማሰራጨት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ተጠምዷል። በተመሳሳይ ሐማስ ሆን ብሎ ሰብዓዊ እርዳታ ሊያገኙ በሚመጡ ንፁኃን ላይ ፍጥጫ እና ጉዳትን ለመጨመር እየሰራ ነው" ብለዋል።

የእስራኤል ጦር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደገለጸው እርዳታ ለመቀበል በሚጠብቁበት ወቅት ሰላማዊ ሰዎች የተጎዱባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ አምኖ "በተቻለ መጠን በሕዝቡ እና [በእስራኤል] ኃይሎች መካከል ሊኖር የሚችለውን ፍጥጫ" ለመቀነስ እየሰራሁ ነው ብሏል።

እርዳታን የማስተባበር ኃላፊነት የተጣለበት የእስራኤል ጦር አካል ኮጋት ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው እስራኤል "በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት እየሰራች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ለማመቻቸት ጥረቶችን እየመራች ነው" ብሏል።

የጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን ቃል አቀባይ በበኩሉ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ሥራውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቦ፣በተጨማሪም በግዛቱ ውስጥ የእርዳታ አቅርቦቶችን ማከፋፈል "በማቆም" ወቅሷቸዋል።

ቻፒን ፋይ ለጋዜጠኞች በድንበር ማቋረጫዎች አካባቢ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እርዳታዎችን ባለማከፋፈላቸው የተነሳ "ሲበሰብስ" መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት እንዳስታወቀው በድንበር አካባቢ 700 እርዳታ የያዙ የጭነት መኪናዎች በተባበሩት መንግሥታት እንዲወሰዱ እየጠበቁ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀጠለው ግጭት፣ እስራኤል በጣለችው የሰብዓዊ እንቅስቃሴ ገደብ እና በነዳጅ እጥረት ምክንያት እርዳታዎቹን ለመውሰድ እና ለማከፋፈል እንደሚቸገር አስታውቋል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ገድሎ 251 የሚሆኑትን ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከፍቷል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 59,029 ሰዎች መገደላቸውን የግዛቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።