አሜሪካ፤ የጋዛ ጥቃትን በመተቸት በሚታወቁት የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያ ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ወታደራዊ ጥቃት፤ በድፍረት በመተቸት የሚታወቁትን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ራፖርተር ፍራንቼስካ አልባኔሴ ላይ ማዕቀብ ጣለ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እርምጃውን ልዩ ራፖርተሯ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ካላቸው ድጋፍ ጋር አያይዘውታል።
የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የተወሰኑ ዳኞች በአሜሪካ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ይታወሳል።
ሩቢዮ፤ የትራምፕ አስተዳደር አልባኔሴ ላይ ማዕቀቡን የጣለው አይሲሲ አሜሪካን ወይም እስራኤላውያንን ለመክሰስ በሚያደርገው ጥረት በቀጥታ በመሳተፋቸው መሆኑን በመግለጽ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ራፖርተር ሆና ለማገልገል ብቁ አይደሉም በማለት ወንጅለዋቸዋል።
ማዕቀቡ አልባኔሴ ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ የሚያግዳቸው ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ያላቸውን ማንኛውንም ንብረት እንዳያንቀሳቅሱም ያግዳል።
አልባኔሴ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት ማዕቀቡን በሚመለከት በቀጥታ ባይናገሩም "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዚህ ቀንም ሁልጊዜ እንደማደርገው በፍትህ ጎን በፅኑ እና በአሳማኝ ሁኔታ እቆማለሁ" ብለዋል።
በጣሊያን የተወለዱት ልዩ ራፖርተሯ ከዚህ በፊት ለአይሲሲ የጻፏቸውን የድጋፍ መልዕክቶች ዳግም በማጋራት፤ ችሎቱን ከመሰረቱ አገራት መካከል መገኘታቸውን ጠቅሰው ጠበቆች ዳኞች "ፍትሕን ከፍ ባለ ዋጋ ብዙ ጊዜ በራሳቸው ሕይወት ጭምር ይከላከላሉ" ብለዋል።
"ይህንን ባህል ለማክበር አስባለሁ" ሲሉ በልጥፋቸው ላይ ጽፈዋል።
አልባኔሴ ለቢቢሲ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ነገር ግን አልጀዚራ ማዕቀቡን "የማፊያ ዓይነት የማስፈራሪያ ዘዴዎች" ሲሉ መግለጻቸውን ዘግቧል።
የትራምፕ አስተዳደር በአይሲሲ ላይ ዘመቻ ከከፈተ ወዲህ አራቱ ዳኞች ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን አሁን ደግሞ የችሎቱን ውሳኔ ደግፈው የቆሙ ላይ በተመሳሳይ ማዕቀብ መጣል ጀምሯል።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ዓመት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በጋዛ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎ አሜሪካ እርምጃውን የወሰደች ሲሆን፤ እስራኤል ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
ሩቢዮ በተጨማሪም፤ አልባኔሴን "ያለ ሀፍረት ፀረ ሴማዊነትን አሳይተዋል፤ ሽብርተኝነትን እንደሚደግፉ እና ለዩናይትድ ስቴትስ፣ ለእስራኤል እና ለምዕራቡ ዓለም ያላቸውን ንቀት አሳይተዋል" ሲሉ ከስሰዋል።
እርምጃው የእስራኤል ጦር በጋዛ በፈጸማቸው ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባደረሰው የሞት አደጋ መጠየቅ አለበት በሚሉ ወገኖች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊያስነሳ ይችላል።
ልዩ ራፖርተሯ፤ የምዕራባውያን መንግሥታት በእስራኤል ወረራ ስር በሚገኙ የፍልስጤም ግዛቶች ለፍልስጤማውያን መብት ድጋፍ ለማድረግ በቂ ጥረት እያደረጉ አይደለም በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።
የአልባኔሴ ግልጽ አቋም፤ የእስራኤል እና የአሜሪካ መሪዎች ፖሊሲዎቻቸውን የሚተቹትን ዝም ለማሰኘት በፀረ ሴማዊነት መወንጀልን እንደ መሣሪያ ይጠቀማሉ ሲሉ በሚከሷቸው ሰዎች መካከል ከፍተኛ ድጋፍን አግኝቷል።
ተቺዎቿ ደግሞ አልባኔሴ በ2014 "የአይሁድ ወትዋች ቡድኖች" የአሜሪካ መንግሥት እስራኤል እና ፍልስጤማውያንን በተመለከተ በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ ሲሉ የተናገሩትን ይጠቅሳሉ።
ራፖርተሯ በወቅቱ ያንን በማለታቸው መጸጸታቸውን ተናግረው ፀረ ሴማዊ ነው የሚለውን ግን ውድቅ አድርገዋል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ኃላፊ እና የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ራፖርተር አግነስ ካላማርድ በአልባኔሴ ላይ ማዕቀብ መጣሉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
"በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት እንዲሁም በሕግ ላይ በተመሰረተ ስርዓት እና በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያምኑ አካላት በሙሉ በፍራንቼስካ አልባኔሴ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተጽዕኖ ለማቃለል እና ለማገድ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
ሩቢዮ፤ አልባኔሴ ለበርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች "የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ" በመጻፍ ለዩናይትድ ስቴትስ ያላቸውን ንቀት አሳይተዋል እንዲሁም መሠረተ ቢስ ውንጀላ በማቅረብ እና አይሲሲ በኩባንያዎቹ እና በአመራሮቻቸው ላይ ክስ እንዲመሠርት ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል ብለዋል።
"ብሔራዊ ጥቅማችንን እና ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጦርነት ዘመቻዎችን አንታገስም" ሲሉ ሩቢዮ ተናግረዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አልባኔሴ ለበርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በጻፉት ደብዳቤ በጋዛ እና በወረራ በተያዘው የዌስት ባንክ በሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ተባባሪ የመሆን ስጋት እንዳላቸው በማስጠንቀቅ ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን ንግድ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ኩባንያዎቹ በወረራ በተያዙት የፍልስጤም ግዛቶች "በሕገ ወጥ ወረራ ከተያዙት አካባቢዎች ከእስራኤል ኢኮኖሚ፣ በአፓርታይድ እና አሁን የዘር ማጥፋት ወንጀል አትራፊ ሆነዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል ሪፖርቱን "መሠረተ ቢስ" ስትል ውድቅ አድርጋ፣ "የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ይገባል" ብላለች።
አልባኔሴ በየካቲት ወር ዶናልድ ትራምፕ የጋዛን ሰርጥ ለመቆጣጠር እና ነዋሪዎቿን ወደ ሌላ ቦታ ለማፈናቀል ማቀዳቸውን ይፋ ሲያደርጉ ተችተዋል።
"ይህ ሕገ ወጥ፣ ኢ ሞራላዊ እና ... ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት የጎደለው ነው፤ ምክንያቱም የቀጠናውን ቀውስ የበለጠ የከፋ ያደርገዋል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።
ማዕቀቡ ይፋ የተደረገው ኔታንያሁ ረቡዕ ዕለት በፔንታጎን ደማቅ አቀባባል ከተደረገላቸው በኋላ ነው።
አልባኔሴ ከዚህ ቀደም በእርሳቸው ላይ ተመሳሳይ ውንጀላዎች ሲቀርቡ ውድቅ አድርገው ነበር።
በጥቅምት፤ "እነዚህን አስተያየቶች እና እነሱ የሚያራምዱትን ስም ማጥፋት በቀላሉ አልመለከተውም፤ ግን በተመሳሳይ ጊዜ ፣ ይህ በእኔ ላይ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ምክንያቱም የቀድሞ ባልደረቦቼ ስለነሱ እንዳልሆነ ያውቃሉ።
"እንዲሁም እነዚህ አባል አገራት [የፀረ ሴማዊነት ውንጀላዎችን የሚያቀርቡ] ለዓለም አቀፍ ሕግ ተገዢ ለመሆን ምንም ያደረጉት ነገር እንደሌለ አውቃለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአልባኔሴ ቢሮ በጉዳዩ ላይ አስተየየት እንዲሰጥ ተጠይቆ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ወደ 125 የሚጠጉ አገራት አይሲሲን ያቋቋሙ ሲሆን በአባልነታቸው የፍርድ ቤቱን ውሳኔዎች የማጽናት ግዴታም አለባቸው።
አሜሪካ እንደ እስራኤል ሁሉ የፍርድ ቤቱ አባል አይደለችም።
በጋዛ ጦርነ ከእስራኤል ጎን የቆመችው አሜሪካ በኔታንያሁ ላይ የወጣውን የእስር ማዘዣ በመቃወም አጋርነቷን አሳይታለች።
ብዙ የአውሮፓ አገራት ግን የፍርድ ቤቱን ነፃነት እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ገድሎ እና 251 ሰዎች ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ዘመቻ ከፍቷል።
የሐማስ አስተዳደር የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 57,575 ሰዎች ተገድለዋል።
አብዛኛው የጋዛ ሕዝብም ብዙ ጊዜ ተፈናቅሏል።
ከ 90 በመቶ በላይ ቤቶች የወደሙ ሲሆን የጤና አጠባበቅ፣ የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
በጋዛ የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድሃኒት እና የመጠለያ እጥረት አለ።















