በፕሬዝዳንት ትራምፕ ዕቀባ የተጣለበት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሥራው ምንድን ነው?

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አርማ

የፎቶው ባለመብት, ICC

የምስሉ መግለጫ, ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አርማ

ጋዛ ውስጥ በተካሄደውን ጦርነት ወቅት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ተፈጽመዋል ባለው የጦር ወንጀሎች በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ላይ ባለፈው ዓመት ያወጣውን የእስር ማዘዣን የተቃወሙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ላይ ዕቀባን ጥለዋል።

ይህ የትራምፕ ዕቀባ ይፋ የሆነው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ በነበረበት ጊዜ ነው። አሜሪካ ፈራሚ ባልሆነችበት በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሠራተኞች ላይ እገዳው የተጣለው ፕሬዝዳንቱ በፈረሙት ትዕዛዝ አማካይነት ነው።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመመለሳቸው በፊት ፍርድ ቤቱ በወዳጃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን "ሕገወጥ እና መሠረት የሌለው ተግባር" ሲሉ ኮንነውታል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት ከ1200 በላይ እስራኤላውያን መገደላቸውን ተከትሎ በጋዛ ላይ በተከፈተው የአጸፋ ዘመቻ ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በዚህ ጦርነት ምክንያትም ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች ምክንያት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሁም የሐማስ ጦር አዛዥ ላይ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።

ይህ የፍርድ ቤቱ የእስር ትዕዛዝ የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ታጣቂውን ሐማስ በአቻነት የሚያይ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ያሉት ትራምፕ፣ ውሳኔው በአሜሪካ ዜጎች እና በወዳጇቿ ላይ የሚደረገውን ምርመራ በሚያግዙ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸወቅ ላይ የገንዘብ እና የቪዛ ዕቀባ የሚያደርግ ነው።

ከዚህ ቀደም በአብዛኛው በአፍሪካውያን መሪዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል በሚል ሲተች የነበረው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ባለፉት ዓመታት በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በታሊባን መሪዎች እና በሚያንማር ወታደራዊ መሪ ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።

ለመሆኑ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዓላማው እና ተግባሩ ምንድን ነው?

መቀመጫውን ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ ያደረገው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች እና በጦር ወንጀል የሚጠየቁ ግለሰቦችን እና መሪዎችን የመክሰስ ሥልጣን ያለው ዓለም አቀፍ ችሎት ነው።

ወንጀል የፈጸሙ መሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ፍርድ ቤት ለማቋቋም ከአስር ዓመታት በላይ ጥረት ሲደረግ ቆይቶ ነው እአአ በ2002 የተቋቋመው።

በዩጎዝላቪያ ጦርነቶች እና የሩዋንዳ የዘር እልቂትን ተከትሎ የዓለም መሪዎች ፍርድ ቤቱ እንዲቋቋም ግፊት አድርገዋል።

ፍርድ ቤቱን ያቋቋመው የሮም ስምምነት በ124 አገሮች ጸድቋል። አሜሪካ ግን የለሁበትም ካሉት አገሮች አንዷ ሆናለች።

ፍርድ ቤቱ ምን ለማድረግ ተቋቋመ?

ፍርድ ቤቱ እስኪቋቋምበት ጊዜ ድረስ ጊዜያዊ ፍርድ ቤቶች እየተሰየሙ በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የፈጸሙትን ለፍርድ ለማቅረብ ተሞክሯል። አይሲሲ የተቋቋመው ይህንን ክፍተት ለመሙላት ነው።

የአንድ አገር ፍርድ ቤት መክሰስ በማይችልበት ወይም በማይከስበት ጊዜ ብቻ ጣልቃ የሚገባ የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ የቀረበ ችሎት ነው።

ሌሎች ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች የሉም?

ከዓለም የወንጀል ፍርድ ቤት በተጨማሪ ሌሎችም ችሎቶች አሉ። ነገር ግን የተለያዩ ሥራዎች ያላቸው ወይም ኃላፊነታቸው የተገደበ ነው።

ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት አንዳንድ ጊዜም የዓለም ፍርድ ቤት ተብሎ የሚጠራው (አይሲጄ) በመንግሥታት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ይመለከታል። ግለሰቦችን ግን መክሰስ አይችልም።

ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እና ሩዋንዳ በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ግለሰቦችን ለፍርድ አቅርበው ነበር። እነዚህ ግን በእነዚያ ችሎቶች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ብቻ የተፈጸሙ ናቸው።

ከዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች በተለየ መልኩ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ቋሚ ፍትሕ አካል ነው።

የሚመለከታቸው ጉዳዮች በጊዜ ገደብ የተወሰኑ ናቸው?

ፍርድ ቤቱ ወደ ኋላ ተመልሶ ጉዳዮችን የመመልከት የዳኝነት ሥልጣን የለውም። የሮማ ስምምነት ከጸናበት ከሐምሌ 2002 ወዲህ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ማስተናገድ ይችላል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን ባጸደቁ አገራት ውስጥ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ወይም ዜጎች ወይም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ሲመራለት ብቻ የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል።

ስኮትላንዳዊው የሕግ ባለሙያ ካሪም ኻን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዋና ዐቃቤ ሕግ ስኮትላንዳዊው የሕግ ባለሙያ ካሪም ኻን

ፍርድ ቤቱ ምን ዓይነት ጉዳዮችን ይከታተላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ብይን የሰጠው እአአ በ2012 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው የሚሊሻ መሪ ቶማስ ሉባንጋ ላይ ነው።

ግለሰቡ ሕጻናትን በጦርነት ውስጥ በማሳተፍ የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሎ 14 ዓመታት ተፈርዶበታል።

በ2011 በነፍስ ማጥፋት፣ በመድፈር፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ስደት እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች የተከሰሰው የአይቮሪ ኮስት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሎረን ባግቦ ትልቅ ስም የነበረው እና በፍርድ ቤቱ የቀረበ ግለሰብ ለመሆን በቅቷል።

እአአ ከ2007 ከምርጫው በኋላ 1200 ሰዎች ከሞቱበት የጎሳ ግጭት ጋር በተያያዘ በ2011 በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች የተከሰሱት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም በፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው ከታየ ታዋቂ ሰዎች ተርታ ይመደባሉ።

በኋላ ላይ አይሲሲ በኬንያታ ላይ የቀረበውን ክስ በታኅሣሥ 2014 አቋርጦታል።

በአይሲሲ ከሚፈለጉት መካከል በሰሜን ኡጋንዳ፣ በሰሜን ምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀሰው የሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ (ኤልአርኤ) አማፂ መሪዎች ይገኙበታል።

መሪው ጆሴፍ ኮኒ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን በማፈን እና በጦርነት ውስጥ በማሳተፍ ወንጀል ተከሷል።

ፍርድ ቤቱ በቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ላይ ያልተጠበቀ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

ይህም በሥልጣን ላይ ባሉ የአገር መሪ ላይ የእስር ማዘዣ ሲወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። በ2015 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ የተሳተፉት አልበሽር፤ ከስብስባው በኋላ ከአገር እንዳይወጡ የአገሪቱ ፍርድ ቤት አዟል።

በአይሲሲ ማዘዣ መሠረት መታሰር እንዳለባቸውም ወስኗል።

ነገር ግን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አልበሽርን እንዲወጡ ፈቃድ ሰጣቸው። ፍርድ ቤቱም ደቡብ አፍሪካ የችሎቱን ሕግ ችላ ብላለች ሲል ከሶ ነበር። ደቡብ አፍሪካም በበኩሏ ከአይሲሲ አባልነት እንደምትወጣ ዝታ ነበር።

እአአ በ2023 ደግሞ አይሲሲ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሕጻናት መብት ኮሚሽነር ማሪያ ሎቮቫ ቤሎቫ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

በዩክሬን ወረራ ወቅት የዩክሬን ልጆችን ወደ ሩሲያ በሕገ ወጥ መንገድ ወስደዋል ተብለው ነው የተከሰሱት።

የእስር ማዘዣው የሩሲያው መሪ ዓለም አቀፍ ጉዞ ላይ ችግር ፈጥሯል። ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት በ2023ቱ የብሪክስ ስብሰባ ከተሳተፉ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በቁጥጥር ሥር እንዲያውሏቸው ጫና በርትቶባቸዋው ነበር። በኋላም ፑቲን በስብሰባው ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

አይሲሲ በፍልስጤም ግዛቶች ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች ላይ እአአ በ2021 መደበኛ ምርመራ ጀምሯል።

የፍልስጤም አስተዳደር በእስራኤል ጦር የተፈጸመ የጦር ወንጀል ነው ያለውን ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት መሠረት የፍልስጤሙ ሐማስ እና የእስራኤል ወታደሮች የጦር ወንጀል መፈጸማቸውን የሚያሳይ ማስረጃም አግኝቷል።

ጆሴፍ ኮኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጆሴፍ ኮኒ

አፍሪካ ላይ ያነጣጠረ መድልዎ

አይሲሲ በተለይም በአፍሪካ ኅብረት በከፍተኛ ደረጃ ይተቻል። ምክንያቱ ደግሞ በአፍሪካ ላይ ትኩረት አድርጓል በሚል ነው።

በፍርድ ቤቱ የ22 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ክስ ያቀረበው ከአፍሪካ በመጡ ግለሰቦች ላይ ብቻ ነው።

አይሲሲ ምንም ዓይነት አድልዎ የለም ሲል ያስተባብላል።

የኤልአርኤ ጉዳይ በኡጋንዳ አንዳንዶቹ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ጥቆማ የቀረቡለት መሆኑን በምሳሌነት አንስቷል።

የጋምቢያዊቷ የቀድሞ የአይሲሲ ዋና ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ፍርድ ቤቱ ወንጀለኞችን በመክሰስ አፍሪካን እየረዳ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

“አይሲሲ ከአፍሪካ ጋር እየሠራ ነው። ለአፍሪካውያን ተጎጂዎችም እየሠራ ነው። ስለዚህ የአፍሪካ ኅብረት ይህን መቃወም ያለበት አይመስለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።

ችሎቱ ተጠርጣሪዎችን እንዴት ለፍርድ ያቀርባል?

አይሲሲ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ የሚይዝ የራሱ የፖሊስ ኃይል የለውም። ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እና ወደ ሄግ ለማዘዋወር የአገራትን የፖሊስ አገልግሎቶችን ይጠቀማል።

የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት አልበሽር ከአገር እንዳይወጡ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም መንግሥት ግን ሽሮታል።

የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ የራሱን ምርመራ በሚያደርግበት ወቅት አባል አገራት የአይሲሲን የእስር ማዘዣ እንዳይፈጽሙ አዟል።

አልበሽር ከፍርድ ቤቱ መያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አልበሽር ከፍርድ ቤቱ መያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል

ሥርዓቱ እንዴት ይሠራል?

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ወይም በአንድ አገር አቤቱታ ከቀረበ ዐቃቤ ሕግ ምርመራ ይጀምራል።

ገለልተኛ እርምጃ ሊወስዱ ቢችሉም ግን ክሱ በዳኞች ቡድን መጽደቅ አለበት።

ዐቃቤ ሕግም ሆነ ዳኞች የሚመረጡት በፍርድ ቤት ውስጥ አባል በሆኑ ክልሎች ነው። አርጀንቲናዊው ሉዊስ ሞሪኖ ኦካምፖ የፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ዋና ዐቃቤ ሕግ ነበሩ።

እያንዳንዱ አባል አንድ ዕጩ ዳኛ የማቅረብ መብት አለው።

ከፍርድ ቤቱ ጋር ለመተባበር ማን ተስማማ?

የሮም ስምምነት እስካሁን በ124 አገራት እና ግዛቶች ጸድቋል። ተጨማሪ 34 ግዛቶ ፈርመዋል ወይም ደግሞ ወደፊት ሊያጸድቁት ይችላሉ ተብሏል።

እስካሁን ድረስ ስምምነቱን ያጸደቁት ሦስት የአረብ አገራት ብቻ ናቸው። እነሱም ዮርዳኖስ፣ ጂቡቲ እና ኮሞሮስ።

ዩናይትድ ስቴትስ ለምን አባል አልሆነችም?

አሜሪካ የፍርድ ቤቱ አባል ብትሆን ወታደሮቿ በፖለቲካዊ ምክንያት ዒላማ ሊሆኑ ወይም ሐሰተኛ ክስ ሊቀርብባቸው እንደሚችል ተከራክራለች።

የተለያዩ ጥበቃዎች እንደሚደረጉም ተነግሮ ነበር። ቢል ክሊንተን በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው መገባደጃ ላይ ካከናወኗቸው ተግባራት በአንዱ ውሉን መፈረም ቢሆንም በአገሪቱ ኮንግረስ ተቀባይነት አላገኘም።

የቡሽ አስተዳደር ደግሞ ፍርድ ቤቱን በጽኑ ተቃውመዋል።

በፍርድ ቤቱ ያለመከሰስ መብት እስካልተሰጣቸው ድረስ የዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በቦስኒያ ያሰማራቻቸውን ወታደሮቿን እንደምታስወጣ እስከ ማስፈራራትም ደርሳለች።

ፍርድ ቤቱ በጦርነት የተሳተፉ ሕጻናት ጉዳይን ይመለከታል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፍርድ ቤቱ በጦርነት የተሳተፉ ሕጻናት ጉዳይን ይመለከታል

በኋላም ብዙ ትችት የቀረበበት ውሳኔ ተላለፈ። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እአአ በ2002 ለአሜሪካ ወታደሮች የ12 ወራት ያለመከሰስ መብትን አጎናጸፈ። ይህ መብትም በየዓመቱ ይታደሳል ሲል አከለበት።

አሜሪካ ወታደሮች የኢራቅ እስረኞችን ሲያንገላቱ የሚያሳዩ ምሥሎች መሠራጨታቸውን ተከትሎ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ግፊት የፀጥታው ምክር ቤት ለወታደሮቹ የተሰጠውን መብት እንደማያድስ በ2004 አስታወቀ።

ያለ አሜሪካ ተሳትፎ የፍርድ ቤቱ ሚና ሲዳከም ደጋግሞ ታይቷል። ዋሽንግተን በተለያዩ ጉዳዮች ከፍርድ ቤቱ ጋር ትብብር ስታደርግ ታይታለች።

የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ስለተፈጸመችው የጦር ወንጀል የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ እንዲያካፍሉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማዘዛቸው አንዱ ማሳያ ነው።

ሌሎች ተቃዋሚዎችስ አሉ?

አዎ። በርካታ አገራት ለአይሲሲ ውሳኔ ላለማገዛት የቆረጡ ይመስላሉ። እንደ ቻይና፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ኢንዶኔዢያ እና ቱርክ ያሉ አገራት ስምምነቱን አልፈረሙም።

እንደ ግብፅ፣ ኢራን፣ እስራኤል እና ሩሲያን ጨምሮ ያሉ ሌሎች አገራት ደግሞ ቢፈርሙም በጥርጣሬያቸው እንደገፉበት ነው።

በዚህ ምክንያት በእነዚህ አገራት የተፈጸሙ በሰው ልጆች ላይ ተፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ወንጀሎች በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሎ አይታሰብም።

ፍርድ ቤቱ በ2024 ሁለት የሩሲያ የጦር አዛዦች ላይ የእስር ማዘዣ ቢያወጣም የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አገራቸው ለማዘዣው ዕውቅና አትሰጥም ብለዋል።

የሚሊሻ መሪው ቶማስ ሉባንጋ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሚሊሻ መሪው ቶማስ ሉባንጋ

አይሲሲ ከአገራት የፍትህ ሥርዓት ጋር እንዴት ይጣጣማል?

ስምምነቱን የተቀላቀሉ አገራት ራሳቸው የሚመለከቱትን ወንጀሎች ለፍርድ ቤት ያቀርባሉ። ይህ ካልሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ጣልቃ ሊገባ ይችላል።

አንዳንድ መንግሥታት በራሳቸው የፍትህ ሥርዓት ላይ ለውጦችን ለማድረግ እንዲያስችላቸው ሕግ አውጥተዋል።

ወጪው በማን ይሸፈናል?

የፍርድ ቤቱ ወጪ በአባል አገራት ይሸፈናል። ይህም ለተባበሩት መንግሥታት ከሚያደርጉት መዋጮ ጋር በተመሳሳይ ሕግ የሚወሰን ይሆናል። ይህም በአባል አገራቱ ብሔራዊ ሃብታቸው ላይ የተመሠረተ ነው።

አሜሪካ አባል አለመሆኗ የፍርድ ቤቱን የገንዘብ ድጋፍ በሌሎች ላይ እንዲበረታ አድርጎታል።

ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ብሪታንያ ከፍተኛ ክፍያ ከሚፈጽሙት መካከል ናቸው።