አገራት የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና ለመተባበር ተስማሙ

በአይኤስ የተገደሉ ከ100 በላይ ሰዎች ቀብር ሲፈጽሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት ዓመታት ተፈጽመዋል ከሚባሉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገረው በአይኤስ ኢራቅ ውስጥ ያዚዲ በተባሉ ማኅበረሰቦች ላይ የተፈጸመው ይጠቀሳል። ፎቶው በአይኤስ የተገደሉ ከ100 በላይ ሰዎች ቀብር ሲፈጽሙ።

የዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎችን በመሳሳሉ ዓለም አቀፍ በሚባሉ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል አዲስ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ስምምነቶች በተጨማሪ ከባድ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እና ተፈጽመው ሲገኙም ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ፍርድ ወደሚያገኙበት ተላልፈው እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ሰባ አገራት በፈረሙበት ዓለም አቀፍ የሕግ ትብብር እና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ የመስጠት (Mutual Legal Assistance and Extradition) ስምምነትን ኢትዮጵያ እስካሁን አለመፈረሟ ተገልጿል።

ለሁለት ሳምንት በቆየው እና የበርካታ አገራት ተወካዮች እንዲሁም የሲቪል ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በአውሮፓዊቷ አገር ስሎቬኒያ በተካሄደው በዚህ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ አልተካፈለችም።

በድርድሩ ላይ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲን ወክለው የተገኙት እና በድርጅቱ የሕግ እና ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ፍሰሃ ተክሌ እንዳሉት በስምምነቱ ላይ በርካታ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ የእስያ፣ የላቲን አሜሪካ አገራት ተወካዮች ፊርማቸውን አኑረዋል።

ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ማላዊ፣ ዚምባብዌ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ አይቮሪኮስት፣ ቤኒን እና ግብፅ ይገኙበታል።

ከሦስት ቀናት በፊት ግንቦት 18/ 2015 ዓ.ም በተፈረመው እና “የወንጀል ፍትሕን፣ የሲቪል ፍትሕን የሚያሰፋ ነው” ባሉት ስምምነት ላይ ሁሉም አገራት እንዲሳተፉ ዕድሉ ተሰጥቷል ያሉት አቶ ፍሰሃ፣ “ኢትዮጵያ ተወካይ አልላከችም። ለምን እንዳላከችም አናውቅም” ብለዋል።

ሆኖም ስምምነቱ እስከ አውሮፓውያኑ 2024 የካቲት 24 ድረስ ለፊርማ ክፍት ሆኖ የሚቆይ በመሆኑ አገራት ስምምነቱ ላይ መፈረም፣ መፈረም የማይፈልጉ ነገር ግን ፍላጎት ያላቸው አገራትም አባል መሆን እንደሚችሉ አቶ ፍሰሃ አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር ተያይዞ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በተፈፀሙ ጅምላ ጭፍጨፋዎች በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸው ይታወቃል።

በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች አሳውቀዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ኮሚሽኑን ከምሥረታው ጀምሮ ከመቃወም ባለፈ በጀት እንዳያገኝ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ እንዲበተን የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ለኅብረቱ አባላት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ስምምነቱ ምን ይላል?

እንደ አቶ ፍሰሃ ከሆነ ስምምነቱ የሕግ እርዳታ እንዲኖር ለማስቻል እና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ለመስጠት የሚረዳ የትብብር ስምምነት ነው።

በዚህ ስምምነት መሠረት በዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በጅምላ ጭፍጨፋ፣ በሰብዓዊ ወንጀሎች፣ በጦር ወንጀሎች፣ በማሰቃየት፣ ሰዎችን በመሰወር እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ አገራት እርስ በርስ ይተባበራሉ።

አገራቱ ማስረጃ በመቀባበል፣ በምርመራ ሂደት በመተባበር፣ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ከፈፀሙበት አገር ወደ ሌላ አገር ተጉዘው ከሆነ ለፍርድ ወደሚያቀርባቸው አገር አሳልፎ በመስጠት አሊያም ባሉበት አገር ለፍርድ እንዲቀርቡ እና እንዲጠየቁ ለማድረግ ያስችላል።

ስምምነቱ ዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሥራን የሚደግፍ እንዲሁም ተጨማሪ የፍትሕ ሥርዓትን የሚፈጥር ነው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ሸሽተው በተገኙበት አገር ፍርድ መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ ያመቻቻል።

ስምምነቱን ባልፈረሙ አገራት ወንጀል የፈፀሙስ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ፍሰሃ እንደሚሉት ስምምነቱን ባልፈረሙ አገራት ውስጥ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ወደ ሌላ አገር ሲሄዱ በዚህ ስምምነት መዳኘታቸው አይቀሬ ነው።

በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ወንጀሉ ከተፈፀመበት አገር ወጥተው የዚህ ስምምነት አባል አገራት ግዛት ላይ ከተገኙ በስምምነቱ መሠረት ይዳኛሉ።

ምን አልባት የስምምነቱ አባል ያልሆነው አገር አልተባበርም ቢል እንኳን ምርመራውን እና የፍርድ ሒደቱን ከማጓተት ውጪ ስምምነቱን ተፈፃሚ ከመሆን አያግደውም።

ከሌሎች ዓለም አቀፍ መሰል ስምምነቶች ምን ልዩ ያደርገዋል?

በጦር ወንጀሎች እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የተጠረጠሩትን ተጠያቂ ለማድረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል፤ እርስ በርስ ለመተባበር የተስማሙ አገራትም አሉ።

ከእነዚህ መካከል ከሁለተኛው ከዓለም ጦርነት በኋላ በጦር ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና የጦር አዛዦችን ለመክሰስ የተቋቋሙት የኑረንበርግ እና የቶኪዮ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤቶች ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም በሩዋንዳ እና በዩጎዝላቪያ የተፈፀሙ የዘር ጭፍጨፋዎች፣ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተጠረጠሩትን ለመጠየቅ በተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመው ፍርድ ቤት፣ ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ለማቋቋም የተደረሰው የሮም ስምምነትን መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ በአብዛኛው የሁለትዮሽ ስምምነቶች ናቸው።

በአዲሱ ስምምነት ግን ከ70 በላይ አገሮች በተጠቀሱት ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ግዛታቸው ውስጥ ከተገኙ ለፍርድ ለማቅረብ እና ለዚህም ለመተባበር የተስማሙበት ነው።

ስምምነቱ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ከአገር በመውጣት ከፍርድ ተጠያቂነት እንዳያመልጡ ያስችላል ተብሎ ይታመናል።

በዚህ ስምምነት መሠረትም ያለመከሰስ መብት ካላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት [የግዛት አስተዳዳሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ . . .] ውጪ በወንጀል የተጠረጠሩ ተጠያቂ ይሆናሉ።

ከዚህም ባሻገር ስምምነቱ መሰል ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ቀድሞ የሚያስጠነቅቅ ነው።

ይህን ስምምነት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች በብዙ መጠን እንደተባዙ አድርጎ ማሰብ ይቻላል ይላሉ አቶ ፍሰሃ የዚህን ስምምነት ጠቀሜታ ሲያስረዱ።

አክለውም ስምምነቱ የወንጀለኞች የማምለጫ መንገዶችን የሚያጠብ እና የተጎጂዎችን ፍትሕ የማግኘት ዕድልን የሚሰፋ ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተጎጂዎች ካሳ የሚያገኙበትን ሁኔታም ስምምነቱ ያስቀምጣል።