የትዕግስት አሰፋን የዓለም ክብረወሰን በእጇ ያስገባችው ኬንያዊት አትሌት በአበረታች ዕጽ ምክንያት ታገደች

ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ችፕንጌቲች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ችፕንጌቲች

በሴቶች ማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ችፕንጌቲች ከማንኛውም የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ በጊዜያዊነት ታገደች።

የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒቲ ይፋ እንዳደረገው የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ሩት ችፕንጌቲች መጋቢት ወር ላይ በተደረገላት ምርመራ ሀይድሮክሎሮቲያዛይድ የተባለ ንጥረ ነገር ተገኝቶባታል።

ችፕንጌቲች በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን የማራቶን የዓለም ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ 56 ሰከንድ በእጇ ማስገባቷም ይታወሳል፡፡

ሀይድሮክሎሮቲያዛይድ (ኤችቲዜድ) በሰውነት ውስጥ የሚከማች ፈሳሽ እና የደም ግፊትን ለማከም የሚያገለግል ሲሆን በዓለም አቀፉ ዶፒንግ ኤጀንሲ መመርያ መሰረት የተከለከለ ነው።

ችፕንጌቲች በቺካጎ በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ እአአ በ2023 ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በሁለት ደቂቃ ያህል ማሻሻል ችላ ነበር።

ሀይድሮክሎሮቲያዛይድ በሽንት ምርመራ ወቅት የሚታወቅ ሲሆን በአንድ ሚሊ ሊትር ውስጥ 20 ናኖግራም ብቻ መኖር እንዳለበት በስፖርት የተከለከሉ አበረታች መድኃኒቶችና ቅመሞች የሚዘረዝረው መመርያ ያዝዛል።

ችፕንጌቲች ናሙና ውስጥ ግን 3800 ናኖ ግራም /ሚሊ ነው።

ችፕንጌቲች ውጤቱ ይፋ በተደረገበት ሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒቲ ያልታገደች ቢሆንም ምርመራው በቀጠለበት ወቅት ግን በፈቃደኝነት በጊዜያዊነት ራሷን ማግለል መርጣለች።

የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒቲ ኃላፊ ብሬት ክሎዚየር "በቀጣዮቹ ወራት ኤአይዩ ምርመራውን የሚቀጥል ሲሆን እና አትለሌቷ እንድታውቀው በማድረግ የራሱን ጊዜያዊ እገዳ ጥሏል" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በተደረገው የቺካጎ ማራቶን 2 ሰአት ከ09 ደቂቃ 56 ሰከንድ በመግባት የዓለም ክብረ ወሰንን በእጇ ያስገባችው የ30 ዓመቷ አትሌት በ2017 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ በእንግድነት ተገኝታ ነበር።

የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒቲ ይፋ እንዳደረገው ድጋሚ ምርመራ እስካልተደረገላት ድረስ ከየትኛውም ውድድር ለጊዜው መታገዷን አሳውቋል።