በናኦሚ ግርማ ተይዞ የነበረውን የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች የዝውውር ክፍያ ክብረ ወሰንን ለአርሰናል የፈረመችው ካናዳዊት ሰበረች

ካናዳዊቷ አጥቂ ኦሊቪያ ስሚዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካናዳዊቷ አጥቂ ኦሊቪያ ስሚዝ በሴቶች የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እጅግ ውድ ተከፋይ ሆናለች

ካናዳዊቷ አጥቂ ኦሊቪያ ስሚዝ በሴቶች እግርኳስ ታሪክ ሪከርድ በሆነ 1 ሚሊዮን ፓውንድ (ከ1.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ) የዝውውር ዋጋ ከሊቨርፑል በመልቀቅ ለአርሰናል ሴቶች ቡድን ፊርማዋን አኖረች።

በዚህም በሴቶች የእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛውን ክፍያ በማግኘት ወደ ሌላ ክለብ የተዘዋወረች ተጫዋች ለመሆን ችላለች።

በ15 ዓመቷ የመጀመሪያዋን ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያደረገችው የ20 ዓመቷ ወጣት ከቻምፒየንስ ሊጉ ባለቤት ጋር የአራት ዓመት ኮንትራት ፈርማለች።

የስሚዝ ፊርማ ቼልሲዎች በጥር ወር ቤተሰቦቿ ኢትዮጵያዊ የሆኑትን አሜሪካዊቷ ተከላካይ ናኦሚ ግርማን ከሳንዲያጎ ዌቭ በ900 ሺህ ፓውንድ ባስፈረሙበት ወቅት የተከፈላትን ከፍተኛ የገንዘብ ክብረ ወሰን የሰበረ ነው።

ስሚዝ "ለአርሰናል መፈረም ትልቅ ዕድል እና ክብር ነው" ብላለች።

የ20 ዓመቷ ኦሊቪያ ስሚዝ ፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበ ክለብ ወደ ሊቨርፑል የተቀላቀለችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።

ኦሊቪያ ከመርሲሳይዱ ክለብ ጋር ቀሪ የሁለት ዓመት ውል ቢኖራትም ሊቨርፑል የቀረበለትን ከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ ውድቅ ማድረግ አልቻለም።

ኦሊቪያ በሊቨርፑል ማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሊቨርፑል ወደ አርሰናል የተዘዋወረችው ኦሊቪያ

"ሕልሜ እዚህ እንግሊዝ እና አውሮፓ ውስጥ ለታላላቅ ቡድኖች መጫወት ነው፤ እናም ይህንን እዚህ ከአርሰናል ጋር ለመጀመር በመቻሌ ደስተኛ ነኝ" ብላለች።

ስሚዝ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኗ በተሳተፈችባቸው ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን አስቆጥራለች።

ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን 18 ጨዋታዎችን አድርጋ አራት ግቦችን አስቆጥሯለች።

ባለፈው የውድድር ዘመን በሴቶች የእግር ኳስ ጨዋታ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሊቨርፑል ስሚዝ ቡድናቸውን መቀላቀሏ ክለቡን ለማጠናከር ትልቅ ዕድል አድርጎ ተመልክቶታል።

ስሚዝ ምንም እንኳን ማርሻል አርትን ጨምሮ በበርካታ ስፖርቶች ውስጥ የተሳተፈች ቢሆንም፣ እግር ኳስ መጫወት የጀመረው በሦስት ዓመቷ ነበር።

በፖርቹጋል ብሔራዊ የሴቶች ሻምፒዮና ውስጥ አስደናቂ የውድድር ዘመን ካሳለፈች በኋላ በ19 ዓመቷ ነው ሊቨርፑልን የተቀላቀለችው።

በ18 ጨዋታዎች 13 ግቦችን በማስቆጠር 9 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችታ በማቀበል የሊጉ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብላ ተሸልማለች።

በ2019 ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገሯ ብሔራዊ ቡድን በ15 ዓመቷ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገች ሲሆን የካናዳ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በመባልም ተመርጣለች።

ለዝነኛዋ ብራዚላዊት የሴቶች እግር ኳስ ተጫዋች ማርታ ያላትን አድናቆት የምትገልፀው ስሚዝ፣ "ክሪስቲን ሲንክሌርን እና ሮናልዲንሆ አርዓያዎቼ ናቸው" ትላለች።

የአርሰናል የሴቶች እግር ኳስ ዳይሬክተር ክላር ዊትሊ "በጨዋታው ውስጥ ካሉት በጣም ጎበዝ ወጣት ተጫዋቾች አንዷ ነች፤ እና በክለቡ ውስጥ በቀጣይ ለማደግ ትልቅ አቅም አላት" ብለዋል።