ከሳምንት በፊት ጋብቻውን የፈጸመው የሊቨርፑሉ አጥቂ ዲዮጎ ጆታ በመኪና አደጋ ሕይወቱ አለፈ

ጆታ ሳምንት በፊት የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ሲፈጽም

የፎቶው ባለመብት, Diogo Jota via X

የምስሉ መግለጫ, ጆታ ከሳምንት በፊት የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ሲፈጽም

የ28 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የሊቨርፑል አጥቂ ዲዮጎ ጆታ ከወንድሙ ጋር በመኪና አደጋ ሕይወቱ ማለፉን የስፔን መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ከዎልቭስ በ40 ሚሊዮን ፓውንድ ለሊርፑል የፈረመው ጆታ በሰሜን ምዕራብ ስፔን ባጋጠመው አደጋ ሕይወቱ ማለፉ ተነግሯል።

ጆታ ከቀናት በፊት ነበር ከረጅም ጊዜ የፍቅር ጓደኛው ሩት ካርዳሶ ጋር ትዳር የፈፀመው። ጥንዶቹ ሦስት ልጆች አሏቸው።

ዛሞራ በተባለችው የስፔን ግዛት ውስጥ ባጋጠመው አደጋ ፖርቹጋል ውስጥ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች የሆነው የ26 ዓመቱ የጆታ ወንድም አንድሬ ሲልቫም ሕይወቱ አልፏል።

የስፔን ፖሊስ እንዳስታወቀው ወንድማማቾቹ የሞቱት ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ነው።

ጆታ ከሚስቱ እና ከልጆቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Diogo Jota via X

የአደጋው ምክንያትም ሲጓዙበት የነበረው ላምቦርጊኒ መኪና ሌላ መኪናን ለመቅደም በሚሞክርበት ጊዜ ጎማው ፈንድቶ በእሳት በመያያዙ ነው።

ዲጎ ጆታ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ሰኔ 15/2017 ዓ.ም. ከረጅም ጊዜ አጋሩ ሩት ካርዶሶ ጋር ቀለበት በማሰር የጋብቻ ሥነ ሥርኣቱን ፈጽሞ ነበር።

ምንም እንኳን ጥንዶቹ በቅርቡ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ይፈጽሙ እንጂ ቀደም ብለው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።

ጆታ በተገባደደው የውድድር ዘመን ሊቨርፑል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተጨማሪም የአገሩ ፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን በሰኔ ወር መጀመሪያ የአውሮፓው ኔሽንስ ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የተጫዋቹን ህልፈት ተከትሎ የፖርቹጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ "የአገሪቱ እግር ኳስ ስፖርት በአደጋው ምክንያት ክፉኛ ተጎድቷል" ብሏል።

ጨምሮም ጆታ "ወደ 50 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ ከድንቅ ተጫዋችም በላይ ነው። ጆታ በክለብ አጋሮቹ እና በተፎካካሪዎቹ ጭምር የተለየ ሰው ተብሎ የሚገለጽ ነው" ሲል ገልጾታል።

"ሁለት ድንቅ ተጫዋቾችን አጥተናል። የዲዮጎ ጆታ እና የወንድሙ አንደሬ ሲልቫ ህልፈት ለፖርቹጋል እግር ኳስ የማይጠገን ጉዳት ነው። አስተዋጿቸውን በየዕለቱ ለመዘከርም ሁሉንም ነገር እናደርጋለን።"

የፖርቹጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአውሮፓ እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ዩኤፋ የፖርቹጋል ሴት ብሔራዊ ቡድን ለአውሮፓ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ከስፔን ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ ጠይቋል።

ፖርቹጋላዊው የሊቨርፑል ተጫዋች ዴጎ ጆታ ህልፈትን ተከትሎ የአግር ኳስ ክለቦች እና ፌዴሬሽኖች እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም የባህል ሚኒስትር ሊንዳ ናንዲ ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።

ጆታ በኔሽንስ ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዋንጫ ባነሳበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጆታ በኔሽንስ ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዋንጫ ባነሳበት ወቅት