የማንቸስተር ዩናይትድ አዲሱ ስታድየም እና ምላሽ የሚፈልጉ ወሳኝ ጥያቄዎች

የዩናይትድ አዲሱ ስታድየም ዲዛይን

የፎቶው ባለመብት, Foster + Partners

የምስሉ መግለጫ, ክለቡ የአዲሱን ስታድየም ዲዛይን ይፋ አድርጓል

የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ በ2 ቢሊዮን ፓውንድ ግዙፍ ስታድየም ለመግንባት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

ይህ 100 ሺህ ተመልካቾች ይይዛል የተባለው ስታድየም ከወቅቱ የክለቡ ሜዳ ኦልድ ትራፈርድ አጠገብ የሚገነባ ነው።

የቀያዩ ሰይጣኖቹን ባለቤት የሚጋሩት ሰር ጂም ራትክሊፍ "የዓለማችንን ታላቁን የእግር ኳስ ስታድየም መገንባት እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ስታድየሙ መቼ ነው የሚገነባው? የግንባታው ገንዘብስ ከየት ይመጣል? ስታድየሙ ምን ይመስላል? ኦልድ ትራፈርድ ዕጣ ፈንታስ?

ቢቢሲ ስፖርት አነዚህን እና ሌሎች ጥያቄዎችን ይመልሳል።

ግንባታው ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

ማንቸስተር ዩናይትድ የስታድየሙ ግንባታ አምስት ዓመታትን ይወስዳል ይላል። ነገር ግን መሰል ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ለወትሮው ቢያንስ 10 ዓመታትን ይፈልጋል።

ክለቡ እንደሚለው ይህን ያህል ግዙፍ የሆነ ስታድየም በአምስት ዓመታት ለማጠናቀቅ የማንቸስተር መርከብ መተላለፊያን ይጠቀማል።

"ለወትሮው 100 ሺህ ተመልካች የሚይዝ ስታድየም ቆፍሮ ለመሥራት 10 ዓመታት ይወስዳል። ነገር ግን ከመንግሥት ጋር ተባብረን የምንሠራ ከሆነ በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል" ይላሉ ራትክሊፍ።

አዲሱ የዩናይትድ ስታድየም ዲዛይን

የፎቶው ባለመብት, Manchester United

ስታድየሙ እንዴት ይገነባል?

ክለቡ እንዳቀደው ከሆነ የስታድየሙ ግዙፍ አካላት ሌላ ቦታ ተገንበተው በማንቸስተር ካናል (ቦይ) በኩል በመርከብ ተጭነው ወደ ኦልድ ትራፈርድ ይመጣሉ።

ራትክሊፍ እንደሚሉት "በዚህ መልኩ የሚገነባ ከሆነ በፍጥነት ይጠናቀቃል።"

"መሰል ግዙፍ ግንባታዎች የሚሠሩበት ቦታ አለ። ከዚያ በኋላ በመርከብ ወደተለያዩ ክፍለ ዓለማት ይላካሉ።"

የሥነ ሕንፃ ባለሙያው ኖርማን ፎስተር ደግሞ "በ10 ዓመታት የሚጠናቀቀውን ግንባታ በግማሽ አሳጥረነዋል። እንዴት ነው ይህን የምናደርገው? በቅድመ ግንባታ። የግንባታውን ወሳኝ አካላት በማንቸስተር ቦይ በኩል እናመጣዋለን።"

ግንባታው መቼ ይጀመራል?

ግንባታው የሚጀመርበት ቀን እስካሁን ቀን አልተቆረጠም።

ራትክሊፍ የግንባታው ጅማሮ የሚወሰነው መንግሥት በፍጥነት ሥራው እንዲጀመር ይሁንታ ሲሰጥ ነው ይላሉ።

"እኔ እንደማስበው መንግሥት በፍጥነት እንዲጀመር ይፈልጋል። ምክንያቱ በወቅቱ ፓርላማ የሥልጣን ጊዜ ሒደቱን ማየት ይሻሉ። በፍጥነት እንደምንጀምር ተስፋ አለኝ።"

የዩናይትድ የኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሌት ሮሽ እንደሚሉት የክለቡ ኃላፊዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሠሩ ነው።

አዲሱ የዩናይትድ ስታድየም ዲዛይን

የፎቶው ባለመብት, Manchester United

የኦልድ ትራፈርድ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

የወቅቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ ኦልድ ትራፈርድ ዕጣ ፈንታው ምን እንደሆነ እስካሁን ግልፅ ባይሆንም፤ የመቆየቱ ነገር አጠራጣሪ ነው።

የሥነ-ሕንፃ ኩባንያው ፎስተር ኤንድ ፓርትነርስ እንደጠቆመው ኦልድ ትራፈርድ ይፈርሳል።

አዲሱ ስታድየም የሚያርፍበት ቦታ ለኦልድ ትራፈርድ ቅርብ ከመሆኑ አንፃር የመፍረሱ ነገር የማይቀር ይመስላል።

"አዲሱን ስታድየም ከቀድሞው አጠገብ በመገንባት የኦልድ ትራፈርድን ክብር እናስጠብቃለን" ሲሉ ራትክሊፍ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ኦልድ ትራፈርድ እንደማይፈርስ እና ለሴቶች ቡድን እንዲሁም ለታዳጊዎች ጨዋታ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተጠቁሞ እንደነበር ይታወሳል።

የዩናይትድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦማር ቤራዳ ክለቡ ይህን ሐሳቡን እንደሚከልሰው ተናግረዋል።

የዩናይትድ የሴቶች ቡድን በአዲሱ ስታድየም ይጫወታል?

የማንቸስተር ዩናይትድ የሴቶች ቡድን በአዲሱ ስታዲየም ጨዋታውን እንዲያደርግ ዕቅድ አለ።

ቤራዳ እንደሚሉት ክለቡ የሴቶቹን ቡድን ደጋፊዎች ቁጥር በማሳደግ በአዲሱ ስታድየም እንዲጫወቱ ለማድረግ አስቧል።

አክለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስታድየሙ ለሴቶች እና ለወንዶች ቡድን እንዲሆን ተደርጎ እንዲሠራ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

ሮሽ እንደሚሉት ደግሞ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሴቶች ግጥሚያ ሲኖራቸው አነስ እንዲል በማድረግ የተለየ የታዳሚ ስሜት መፍጠር ያስችላል።

አዲሱ የዩናይትድ ስታድየም ዲዛይን

የፎቶው ባለመብት, Manchester United

የግንባታውን ወጪ ማን ይሸፍናል?

ክለቡ የስታድየም ግንባታው ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ ይፋ አላደረገም።

ነገር ግን ከብድር፣ ከግል ኢንቨስትተመንት እና ከራትክሊፍ በሚገኝ ገንዘብ ሊገነባ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ቢሆንም ራትክሊፍ በከፊል ክለቡን ከገዙት በኋላ እያካሄዱ ካሉት የገንዘብ ቁጠባ ጋር ሊጋጭ ይችላል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በአሁኑ ወቅት የአንድ ቢሊዮን ፓውንድ ዕዳ አለበት።

የእግር ኳስ ፋይናንስ ባለሙያው ኪየራን ማጓዬር የቶተንሀም ስታድየምን እንደምሳሌ በማንሳት ዩናይትድም ገንዘብ አያጣም ይላሉ።

"ቶተንሀም በለንደን አዲስ ስታድየም ሲገነባ የወለድ መጠኑ ከ12 ሚሊዮን ወደ 46 ሚሊዮን ፓውንድ አድጎ ነበር። ነገር ግን ከስታድየም ገቢ የሚያገኘው ገንዘብ በ72 ሚሊዮን ሲጨምር ከሌሎች አማራጮች የሚገኘው ገቢ ደግሞ በ155 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍ ብሏል።"

ራትክሊፍ ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ "የገንዘቡ ነገር የሚያሳስብ አይደለም" ብለዋል። አክለው ከሕዝቡ ምንም ገንዘብ እንደማይጠይቁ አሳውቀዋል።

ዩናይትድ አዳዲስ ተጫዋቾችን መግዛት ያቆማል?

ቤራዳ እንደሚሉት ከሆኑ ቡድኑን በፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ ብሎም ዋንጫ እንዲያነሳ ለማስቻል የስታዲየሙ ግንባታ ወጪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለመግዛት እንቅፋት አይሆንም።

አክለው እንደሚሉት ክለቡ አዲስ ስታድየም ለመገንባት ሲል የቡድኑን መልሶ መቋቋም አይነካም።

"የእዚህ ክለብ ትልቁ ሀብቱ ደጋፊዎቹ ናቸው። በዓለም ዙሪያ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ነው። ይህ ደግሞ የገንዘብ ማግኛ አቅም ይፈጥርልናል።"

ማንቸስተር ዩናይትድ የአዲሱ ስታድየም ግንባታ 92 ሺህ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር እና 17 ሺህ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ እንዲሁም ለዩናይትድ ኪንግደም ምጣኔ ሀብት 3 7.3 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያስገኝ አስታውቋል።

ስታድየሙ ሲጠናቀቅ በዓመት ተጨማሪ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚጎበኙት ይገመታል።

በእንግሊዝ ግዙፉ የሆነው ኦልድ ትራፈርድ ስታድየም 74 ሺህ 140 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ቅሬታዎች እየተነሱበት ይገኛሉ።