ማንቸስተር ዩናይትድ በ2 ቢሊዮን ፓውንድ አዲስ ስታድየም ሊገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, MANCHESTER UNITED
ማንቸስተር ዩናይትድ በዩናይትድ ኪንግደም ትልቁ ይሆናል የተባለውን ስታድየም እንደሚገነባ አስታውቋል።
2 ቢሊዮን ፓውንድ ያወጣል የተባለው አዲሱ ስታድየም ኦልድ ትራፈርድ አካባቢ የሚገነባ እና 100 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ነው።
የዩናይትድ አጋር ባለቤት የሆኑት ሰር ጂም ራትክሊፍ "በዓለማችን ግዙፉን ስታድየም" የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረው ነበር።
ስታድየሙ በአምስት ዓመታት ተገንብቶ እንደሚያልቅ ክለቡ አስታውቋል።
ዩናይትድ የስታድየሙን ዕቅድ ይፋ ያደረገው ኦልድ ትራፈርድ ማደስ አሊያም አዲስ ስታድየም መገንባት የሚል ምክክር ካደረገ በኋላ መሆኑ ተሰምቷል።
ኦልድ ትራፈርድ ከአውሮፓውያኑ 1910 ጀምሮ የማንቸስተር ዩናይትድ ስታድየም ሆኖ አገልግሏል።
የሥነ ሕንፃ ኩባንያው ፎስተር ኤንድ ፓርትነርስ ስታድየሙ የዣንጥላ ቅርፅ የሚኖረው እና ግዙፍ አደባባይ እንደሚኖረው አሳውቋል።
አልፎም "ዘ ትራይደንት" የተባለ ከ40 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚታዩ ማማዎች ይኖሩታል።
በአሁኑ ወቅት 1 ቢሊዮን ዕዳ ያለበት ማንቸስተር ዩናይትድ ለሕንፃው ግንባታ ወጪ ገንዘብ ከየት እንደሚያገኝ ይፋ አላደረገም። የክለቡ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኦማር ቤራዳ "ግንባታውን የምናከናውንበት ገንዘብ እንደምናገኝ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የአዲሱ ስታድየም ግንባታ 92 ሺህ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጥር እና 17 ሺህ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ እንዲሁም ለዩኬ ምጣኔ ሀብት3 7.3 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያስገኝ አስታውቋል።
ስታድየሙ ሲጠናቀቅ በዓመት ተጨማሪ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚጎበኙት ይገመታል።
ጂም ራትክሊፍ ላለፉት 115 ዓመታት ያገለገለው ኦልድ ትራፈርድ አሁን ካሉ ዘመናዊ ስታድየሞች ጋር የሚነፃፀር አይደለም ብለዋል።
ራትክሊፍ ግንባታው መቼ እንደሚጀመር ይፋ ባያደርጉም ከመንግሥት ይሁንታ እንዳገኙ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በእንግሊዝ ግዙፉ የሆነው ኦልድ ትራፈርድ ስታድየም 74 ሺህ 140 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ቅሬታዎች እየተነሱበት ይገኛሉ።
ስታድየሙ ከአውሮፓውያኑ 2006 በኋላ ትልቅ የሚባል ማሻሻያ ተደርጎበት አያውቅም።
አዲሱ ስታድየም ግንባታው ሲጠናቀቅ ኦልድ ትራፈርድ ምን ይሆናል የሚለው ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም ለሴቶች ቡድን እና ለታዳጊዎች ጥቅም ላይ እንደሚውል ተነግሯል።












