ኬንያውያኑ ሴት አትሌቶች ኪፕዬጎን እና ቼቤት የዓለም ክብረ ወሰንን ሰበሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት ቅዳሜ፣ በአሜሪና ዩጂን ከተማ ኦሪገን ግዛት በተካሄደው 50ኛው የፕሪፎንቴይን ክላሲክ፤ የ2025 ዩጂን ዳይመንድ ሊግ፤ ኬንያውያኑ ፌዝ ኪፕዬጎን እና ቢትሪስ ቼቤት በአስደናቂ ሁኔታ የዓለም ክብረ ወሰን ሰበሩ።
በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉበት የወንዶች 10 ሺህ ሜትር፣ የሴቶች 5 ሺህ፣ የ800 ሜትር እና የ1500 ሜትር ውድድር ተካሂዷል።
ፌዝ ኪፕዬጎን በራሷ ተይዞ የነበረውን የ1500 ሜትር ክብረ ወሰን ስታሻሽል፣ ቢትሪስ ቼቤት ደግሞ በኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ የተያዘውን የ5000 ሜትር ክብረ ወሰን አሻሽላለች።
ኪፕዬጎን በሴቶች 1500 ሜትር ሦስት ደቂቃ ከ48.68 ሰከንድ በመግባት አሸንፋለች።
በወንዶች 10ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስተኛ በመውጣት አሸንፈዋል።
አትሌት ቢኒያም መሃሪ ውድድሩን በ26:43.82 በመግባት ሲያሸንፍ፣ አትሌት በሪሁ አረጋዊ 26:43.84 በመግባት ሁለተኛ ወጥቷል።
አትሌት ሰለሞን ባረጋ 26: 44.13 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃ ይዟል።
በ800 ሜትር ሴቶች ውድድር አትሌት ፅጌ ዱግማ 1:57.10 በመግባት በአንደኝነት አሸንፋለች ።
በ1500 ሜትር የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮና የሆነችው የ31 ዓመቷ ኪፕዮጎን፣ ይህንን ድል ያገኘችው ርቀቱን ከአራት ደቂቃ በታች በመጨረስ በታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ለመሆን ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ በቀረ በሳምንቱ ነው።
በዚህ ውድድር ላይ ድሪቤ ወልተጂ በ3፡51፡44 በ3 ሰከንድ ዘግይታ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቅቃለች።
ሌላኛዋ ኬንያዊት ቼቤት በኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከሁለት ዓመት በፊት ተይዞ የነበረውን የ5000 ሜትር ክብረ ወሰን ከሁለት ሰከንድ በላይ በማሻሻል በ13፡58.06 ሰዓት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።
ቼቤት የገባችበትን ሰዓት ስትመለከተው ደንግጣለች፤ ባለፈው ዓመት በዩጂን ያስመዘገበችው የ10,000 ሜትሮች ክብረወሰን ላይ ይህንን ደርባ ስትቀዳጅ ደስታ እንደተሰማት ገልፃለች።
ባለፈው ወር ሮም ላይ 14:03.69 ስትሮጥ ክብረ ወሰኑን እንደምትሰብረው ሲገመት ቆይቷል።
የ5000 ሜትር ውድድር ላይ መዲና ኢሳን ጨምሮ 13 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተካፍለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ውድድሩን አላጠናቀቁም።
የ25 ዓመቷ ቼቤት አሁን በ5,000 እና በ10,000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን እና የኦሊምፒክ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ናት።
"ወደ ዩጂን ስመጣ የዓለምን ሪከርድ ለመሮጥ ለመዘጋጀት ነበር የመጣሁት" ብላለች። አክላም "በጣም ደስተኛ ነኝ" ብላለች።
ጉዳፍ ፀጋይ ከኬኒያዊቷ አግነስ ጄቤት ንጌቺ ጋር በመሆን ከቼቤት ጋር ቢፎካከሩም ቼቤት ግን አፈትልካ በመውጣት ክብረወሰኑን ሰብራለች።
ጄቤት ንጌቺ 14:01.29 በመግባት ሁለተኛ ሆና የጨረሰች ሲሆን፣ ይህም ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ነው።
ሁለቱ አትሌቶች በፓሪስ ኦሊምፒክ 17 ሻምፒዮናዎች እና 14 የዓለም ሪከርድ ባለቤቶች በተሞላው ውድድር ላይ ደምቀው ታይተዋል።
ከብሪታንያ አትሌቶች መካከል ማት ሃድሰን ስሚዝ በወንዶች 400 ሜትር አሜሪካውያኑን ክሪስቶፈር ቤይሊ እና ጃኮሪ ፓተርሰን ቀድሞ 44.10 ሰከንድ በመግባት ደምቆ የታየበት ምሽት ነበር።
በወንዶች 100 ሜትር እንዲሁ ብሪታኒያው ዣርኔል ሂዩዝ ጃማይካዊው ኪሻን ቶምፕሰንን ተከትሎ 9.85 ሰከንድ በመግባት ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
በፓሪስ ሆጅኪንሰን የብር ሜዳሊያ ያስገኘችው ኢትዮጵያዊቷ ፅጌ ዱጉማ 1፡57፡10 በሆነ ጊዜ በመግባት አሸንፋለች።
ዲና አሸር ስሚዝ በሴቶች 100ሜ ሰባተኛ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን፣ አሜሪካዊቷ ሜሊሳ ጄፈርሰን ዉደን በ10.75 ሰከንድ በመግባት የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ጁሊን አልፍሬድ ቀድማለች።
የዳይመንድ ሊግ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከመሄዱ በፊት ወደ ሞናኮ ይሸጋገራል።
በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት በፊት የፍጻሜ ውድድሮች ነሐሴ 27 እና 28 በዙሪክ ይካሄዳሉ።















