በናይሮቢ ሊካሄድ የነበረው የጃዋር መጽሐፍ ምርቃት "በደህንነት ስጋት" ምክንያት ተሰረዘ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሩ ጃዋር መሐመድ 'አልጸጸትም' በሚል ርዕስ ሐሙስ፣ ታህሳስ 10/ 2017 ዓ.ም በናይሮቢ ሊያስመርቀው የነበረው መጽሐፍ ከተለያዩ አካላት በደረሱ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን የቢቢሲ ምንጭ ገለጹ።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እኚሁ ምንጭ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት መጽሐፉ የሚመረቅበት ናይሮቢ የሚገኘው የኬንያታ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል መሆኑ ከታወቀ በኋላ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ደርሰዋል ብለዋል።
ዛቻው ማዕከሉን ለሚያስተዳደሩት አካላት በመድረሱ ምርቃቱ መሰረዙን ገልጸዋል።
አንዳንድ ማስፈራሪያዎች የጸጥታ ስጋት እንዳለ በመጥቀስ ለማዕከሉ አስተዳደሪዎች ይደርስ ነበር ብለዋል።
የምረቃው ኮሚቴው የአዳራሹን ጸጥታና ደህንነት ለማስጠበቅ ማረጋገጫ ቢሰጥም እልባት ሊያገኝ አልቻለም።
ነገር ግን ይህ ማስፈራሪያ ተጠናክሮ ረቡዕ፣ ታህሳስ 9/ 2017 ዓ.ም ይፋዊ የሆነ ዛቻ/ተቃውሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት መድረሱን እኚሁ ምንጭ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አደረሰው የተባለው ይፋዊ የሆነው ዛቻ/ተቃውሞ ለየትኛው አካል እንደደረሰ ምንጩ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ ከመንግሥት ደረሰ የተባለውን ዛቻ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።
ቢቢሲ ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጉዳዩን በሚመለከት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ዛሬ ሐሙስ ታሕሳስ 10 2017 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው የመፅሐፍ ምርቃት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
ጃዋር በፌስቡክ ገጹ ላይ "በተሳታፊዎች ብዛት እና በደህንነት ስጋት" ምክንያት የምረቃ አዳራሹ አስተዳደር ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፉን ገልጾ በቅርብ ቀን ተቀያሪ ቦታ እናሳውቃለን ብሏል።
ጃዋር በቅርቡ ለቢቢሲ እንደተናገረው የፖለቲካ ጉዞ እና የሕይወት ታሪኩን በሚመለከት 'አልጸጸትም' በሚል ርዕስ በኦሮምኛ እና በአማርኛ መጽሐፍ ጽፎ አሳትሟል።
ጃዋር ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት መጽሃፉን በኢትዮጵያ ለማስመረቅ እንደሚፈልግ ነገር ግን "...በአገሪቱ መጽሐፍ ማስመረቅ ይቅርና ለመተንፈስ ከባድ ነው" ሲል መናገሩ ይታወሳል።
እንደ የመጽሐፍ ምረቃ አዘጋጆቹ ገለጻ መጽሐፉን ለማስመረቅ የተያዘው ስፍራ ናይሮቢ የሚገኘው የኬንያታ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ነበር።
መጽሐፉን ለምን አሁን ማውጣት አስፈለገ? መጽሐፉ በናይሮቢ የሚመረቀውስ ለምንድን ነው? በሚል ከቢቢሲ የተጠየቀው ጃዋር "ኢትዮጵያ ለማስመረቅ ፍላጎት ነበረኝ" ብሏል።
ሆኖም ግን "ገዢዎቹ ደስተኛ አልነበሩም። አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ለመጽሐፍ ብዬ አምቧጓሮ ውስጥ ለመግባት አልፈለግኩም" ሲልም በጎረቤት አገር መዲና መጽሐፉን ለማስመረቅ የወሰነበትን ምክንያት አስረድቷል።
መጽሐፉን አውሮፓ ለማስመረቅም አስቦ የነበረ ቢሆንም "ኬንያ ያለው ማኅበረሰብ ከእኛ መጀመር አለብህ" ብሎ እንደጠየቀው አክሏል።
በቀጣይ "መጽሐፉን ከማስመረቅ ባሻገር፤ አሁን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ለመወያየት እና ወደፊት ምን መሠራት አለበት የሚለውንም ሐሳብ ለማቅረብ እንዲሁም ለማዳመጥም" ወደ አውሮፓ አገራት እንደሚጓዝ ተናግሯል።
"ጦርነቱ ትንሽ ጋብ ካለ በኋላ መጽሐፍ ቢቀርብ ሰው በተረጋጋ መንፈስ ለማንበብ ዕድል ይኖረዋል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሮች እየተሻሻሉ ሳይሆን እየተባባሱ ነው የሄዱት።
ከዚህ በላይ ብጠብቅም የመሻሻል ተስፋ ይኖረዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ስላልቻልኩ አሁን ለማቅረብ ወሰንኩ። መጽሐፉ ተጠናቆ እንዳለ የሚያውቁ ሰዎችም እንዲቀርብ ጫና ሲያደርጉብኝ ነበር። መጨረሻ ላይ ለማቅረብ ወሰንኩ" ሲልም ፖለቲከኛው ተናግሯል።












