የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባሉ ከአምስት ዓመት በፊት ተቋርጦ በነበረ ክስ ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali/FB
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጸደቁ ሁለት አዋጆች ላይ የሕገ መንግሥት አቤቱታ ካቀረቡ ከቀናት በኋላ የታሰሩት የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ተቋርጦ በነበረ ክስ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባቸው።
አቶ ዮሐንስ፤ በአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉበት ከከተማ ቦታ ሊዝ ጋር የተያያዘ ክስ፤ ከሰባት እስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣ ነው።
ተቃዋሚውን የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ቦዴፓ) ወክለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት የአቶ ዮሐንስ፤ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰኞ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም. ከሰዓት በዋለ ችሎት ነው።
የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር ዋሉት የካቲት ላይ ነበር።
አቶ ዮሐንስ የታሰሩት የክልሉን ሕገ መንግሥት እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች እና የምርጫ ክልሎችን ብዛት ያሻሻሉ ሁለት አዋጆች "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" ከሌሎች ሁለት የምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አቤቱታ ካቀረቡ ከአምስት ቀናት በኋላ ነበር።
የምክር ቤት አባሉ ከታሰሩት አንድ ሳምንት ገደማ በኋላ በተካሄደ አስቸኳይ ጉባኤ ከለላቸው ተነስቷል። ይህ መብት የተነሳው "ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ቅስቀሳ አድርገዋል" እንዲሁም "ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳለው ሚያመለክቱ ሁኔታዎች አሉ" በሚል በመጠርጠራቸው እንደሆነ ተገልጾ ነበር።
የምክር ቤት አባሉ ተጠርጥረውበታል የተባለው ጉዳይ ይህ ቢሆንም "ከዚህ በፊት የተከሰሰበት መዝገብ ስላለ" የሚል ሀሳብም ተነስቶ እንደነበር ቢቢሲ የተመለከተው ቃለ ጉባኤ ያመለክታል።
የምክር ቤት አባሉ መጋቢት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡም የተጠረጠሩት "የክልሉን ሕገ መንግሥት ለመናድ በመንቀሳቀስ"፣ "ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር"፣ እንዲሁም "የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች በመሳደብ" ድርጊቶች እንደሆነ በችሎቱ ውስጥ ተገልጾ ነበር። ይህ መዝገብ በሂደት ላይ ሲሆን እስካሁን ክስ አልተመሠረተም።
አቶ ዮሐንስ በመጋቢት መጨረሻ ደግሞ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣውን አዋጅ በመጣስ ሌላ የክስ መዝገብ ተከፍቶባቸዋል። የክስ መዝገቡ፤ የምክር ቤት አባሉ በ2012 ዓ.ም. በታሰሩበት ወቅት ቀርቦባቸው የነበረ ነው።
በወቅቱ ስምንት ወራትን በእስር ያሳለፉ ሲሆን፣ ክሱም በፍርድ ቤት ክርክር እየተደረገበት ነበር። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ክሱን በማቋረጡ በ2013 ዓ.ም. መጀመሪያ አቶ ዮሐንስ እንደተፈቱ አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላ በድጋሚ የተከፈተው የክስ መዝገብ፤ ከዚህ ቀደም የተቋረጠው እንደሆነ ቢቢሲ ከክስ ሰነዶች ተመልክቷል።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ የምክር ቤት አባሉ ተጠረጠሩት በአሶሳ ከተማ የሚገኝ "328 ካሬ ሜትር የመንግሥት ባዶ ቦታ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኝ" በመያዝ ነው። ይህ ይዞታ አቶ ዮሐንስ በ2006 ዓ.ም. "በግዢ ካገኙት" እና "በስማቸው ሕጋዊ ካስደረጉት" ቦታ አጠገብ የሚገኝ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Ashadeli Hassen
የዐቃቤ ሕግ ክስ "በሕጋዊ መንገድ ከያዘው ይዞ 300 ካሬ ሜትር ቦታ ጋር አካቶ እና አስፋፍቶ በማጠር እና በሕገ ወጥ መንገድ ግንባታ [አካሂዷል]" ሲል ተፈጽሟል ያለውን ወንጀል ያስረዳል።
በዚህም ምክንያት "ከሊዝ አዋጅ ስሪት ውጪ የከተማን ቦታ አስፋፍቶ እና አጥሮ በመያዝ ወንጀል ተከስሷል" ሲል በመዝገቡ ጠቅሷል።
ዐቃቤ ሕግ ክሱን ያቀረበባቸው አንቀጾች፤ የፌደራል መንግሥት በ2004 ዓ.ም. ባጸደቀው "የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ " ላይ የተደነገጉ ናቸው።
ከእነዚህ አንቀጾች አንዱ "ማንኛውም ሰው የከተማ መሬትን በዚህ አዋጅ ከተደነገገው የሊዝ ሥርዓት ውጪ መያዝ አይችልም" በሚል የሰፈረው ነው።
"አግባብ ካለው አካል ፈቃድ" ያላገኙ ሰዎች በሕጋዊነት ከያዙት ይዞታ "ጎን ያለን የከተማ ቦታ አስፋፍቶ መከለልና መጠቀም" እንደማይችሉ የተደነገገው አንቀጽም በክሱ ውስጥ ተጠቅሷል።
ይህ ክስ በድጋሚ የቀረበባቸው አቶ ዮሐንስ በቅድሚያ ያነሱት መከራከሪያ "ያለመከሰስ መብቴ የተነሳው ሕገ መንግሥትን በመናድ በሚል ነው። አንድ ሰው ሊከሰስ የሚችለው ያለመከሰስ መብቱ በተነሳበት ጉዳይ ብቻ ነው" የሚል እንደነበር አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ መከራከሪያ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ግን የተከሰሱበትን ድርጊት አለመፈጸማቸውን በመግለጽ የክስ መቃወሚያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
አቶ ዮሐንስ ይዞታው "በግዢ እንደተገኘ፣ በግዢ ከተገኘ በኋላ ሰነድ አልባ ስለመሆኑ በቀበሌ እና በወረዳ ተረጋግጦ ወደ ማዘጋጃ ተልኮ የፕላን ስሪት ሂደት ላይ መሆኑን" ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን የቤተሰብ አባሉ ጠቅሰዋል።
ይህንን ለማስረዳትም "የግዢ ውል"፣ "የመሬት ግብር ማስረጃዎችን" እና ሌሎች ሰነዶችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል። "11 የመከላከያ ምስክሮችን" እንደቆጠሩም አክለዋል።
ከምስክሮቹ መካከልም "ሽያጩ ሲፈጸም ምስክር የነበሩ ሰዎች" እንዲሁም "ከመሬቱ ግብር መሰብሰባቸውን እና አረጋግጠው ለሚመለከተው አካል መምራታቸውን ያስረዱ የወረዳ ባለሙያዎች" እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ጉዳዩን የሚመለከተው የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነዚህን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች እንዳልተቀበለ የቤተሰብ አባሉ ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹን ውድቅ ሲያደርግ ከጠቀሳቸው ምክንያቶች አንዱ "የግዢ ሂደቱ በሚመለከተው አካል ጸድቆ እውቅና ያላገኘ ነው" የሚል እንደሆነም ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yohannes Tessema
ፍርድ ቤቱ ሰኞ ከሰዓት በዋለው ችሎት አቶ ዮሐንስ በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት "ጥፋተኛ ናቸው" በማለት ውሳኔ እንዳሳለፈ ሦስት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ መሠረት አቶ ዮሐንስ ጥፋተኛ የተባሉበት ድርጊት ከ7 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል።
አዋጁ፤ ማንኛውም ሰው "የከተማ ቦታን አጥሮ ከያዘ፣ ግንባታ ካካሄደበት ወይም ከአዋሳኝ ይዞታው ጋር ከቀላቀለ ከ7 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር 40 ሺህ እስከ ብር 200 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል" በማለት ደንግጓል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ አቶ ዮሐንስ "በ18 ዓመት እስራት እንዲቀጡ" የቅጣት አስተያየቱን ለፍርድ ቤት ማቅረቡን የቤተሰብ አባሉ ተናግረዋል።
አቶ ዮሐንስ የምክር ቤት አባል እንዲሁም በሕግ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን መሆኑን በመጥቀስም በዚህ ሁኔታ ውስጥ "ይህንን ድርጊት መፈጸማቸው በቅጣት ማክበጃነት እንዲያዝለት" መጠየቁንም አክለዋል።
የቅጣት ማቅለያቸውን እንዲያቀርቡ የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው ዝግጁ አለመሆናቸውን በመጥቀስ ሌላ ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል ተብሏል። የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ለሐምሌ 6/2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
የጥፋተኝነት ውሳኔው የተላለፈው አቶ ዮሐንስ "በቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ" የሚያስችል ነጥብን የያዘ ስምምነት በክልሉ ባለሥልጣናት እና በምክር ቤት አባሉ ፓርቲ አመራሮች መካከል በሰኔ ወር መፈረሙ ከተገለጸ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአደራዳሪነት በተገኙበት በዚህ ስምምነት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰንም ተሳትፈው እንደነበር ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በክልሉ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ የሚያስችሉ ተግባራትን በጋራ ለመፈጸም የተፈራረሙት የክልሉ ባለሥልጣናት እና የፓርቲው አመራሮች፤ የእነዚህን ተግባራት አፈጻጸም ተከትሎ አቶ ዮሐንስ እንዲፈቱ እንደተግባቡም ተገልጾ ነበር።















