በቤንሻንጉል ክልል የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ያነሱት የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ተነሳ

የፎቶው ባለመብት, Yohannes Tessema FB
የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ያነሱት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ቅዳሜ፣ መጋቢት 6/ 2017 ዓ.ም ተነሳ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ተሰማ ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣የክልሉን እና የምክር ቤቱን ክብር የሚነኩ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨታቸው ያለ መከሰስ መብታቸው መነሳቱ ተገልጿል።
የቤንሻንጉል ክልል በዛሬው ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አቶ ዮሐንስ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያነሳሳ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሠራጨታቸውና፣ መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከሚጥሩ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አመላካች መረጃዎች መኖራቸውም ተገልጿል።
የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደው በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ያለመከሰስ መብታቸውን ሲያነሳ ለምክር ቤቱ ማብራርያ የሰጡት የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ሐሚድ፣ ግለሰቡ 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 1ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው ውሳኔዎችን ካሳለፈ በኋላ በዚህ ድርጊት መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
የምክር ቤቱ አባል በተጠረጠሩበት ጉዳይ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ የአቶ ዮሐንስ ተሰማ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸው ተገልጿል።
አቶ ዮሐንስ ተሰማ የተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) አባል ሲሆኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት እሁድ የካቲት 30/2017 ዓ.ም. ነበር።
ፖለቲከኛው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሌሎች ሁለት ፓርቲውን የወከሉ የምክር ቤት አባሎች ጋር በመሆን የተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግሥት እና የተወካዮች ብዛት ያሻሻሉት አዋጆች "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አቤቱታ ባቀረቡበት ሳምንት ነው።
የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር እና የምክር ቤት አባል አቶ ዮሃንስ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
አቶ ዮሃንስ ወደ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት የምክር ቤት አባል በመሆናቸው ያገኙት ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መያዛቸውን በመጥቀስ "ለመርማሪ ፖሊሶች ቃል ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሆን እንደሚችልም" ተናግረው ነበር።
ሦስት የምክር ቤት አባላት የካቲት 25 ለሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ ባቀረቡት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ፤ ከ100 ወደ 165 ያደገው የምክር ቤት መቀመጫ ብዛት ለምርጫ ክልሎች የተከፋፈለበት መንገድ "የሕዝብ ብዛትን ሳይሆን የወረዳ ቁጥርን" መሰረት ያደረገ እንደሆነ በመጥቀስ ተቃውመው ነበር።
"ነባር የምርጫ ክልሎች መፍረስ እና አዲስ የምርጫ ክልሎች መመስረት" እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ የተሻሻለበት ሂደትም ጥያቄ የቀረበባቸው ጉዳዮች ናቸው።
የምክር ቤት አባላቱ፤ እነዚህን ለውጦች ያስተዋወቁት ሁለት አዋጆች "ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ ያልነበሩ፣ ያልተደነገጉ እንዲባሉ" እና "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባስገቡት አቤቱታ ጠይቀዋል።
ይህ አቤቱታ ለጉባኤው ከገባ ከሁለት ቀናት በኋላ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ "ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት ለማስገባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል" ያላቸውን "አንዳንድ" የቦዴፓ አመራር እና አባሎችን አስጠንቅቋል።
ከዚህ መግለጫ ከሦስት ቀናት በኋላ አቤቱታውን ካስገቡት የምክር ቤት አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ታስረዋል።
ሐሙስ ዕለት ደግሞ ተሹመውበት ከነበሩበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነት ተነስተዋል።
የክልሉ መንግሥት፤ የመንግሥት ኃላፊነት ከሰጣቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ዮሃንስ፤ ተቋሙን ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከሶስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ መርተዋል።
ሐሙስ ዕለት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ በእስር ላይ ያሉትን አቶ ዮሃንስን ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነት ማንሳታቸውን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።
በምትኩም እስከ ትናንት ድረስ የክልሉን የሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ አብዱልሰላም ኢብራሂም እንደተሾሙ ተገልጿል።












