አንጎላ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ፖለቲከኞችን አላስገባም አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አንጎላ የአገሪቱ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ የተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮችን ወደ አገሯ እንዳይገቡ መከልከሏ ቁጣ አስነሳ።
ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ሞዛምቢክ እና ደቡብ ሱዳን የመጡ ቪዛ ያላቸው እንዲሁም በአገሪቷ ሲደርሱ ቪዛ ለመውሰድ ሲጠባበቁ የነበሩ ፖለቲከኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን፤ በመላው አፍሪካ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰብ የሆነው 'ፕላትፎርም ፎር አፍሪካን ዴሞክራትስ (ፓድ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የታንዛንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ፣ የሞዛምቢኩ ቬንሲዮ ሞንድላን እና የቦትስዋና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢያን ካማን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በዲሞክራሲ ላይ በሚደረገው ጉባኤ እንዲገኙ የአንጎላ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ዩኒታ መጋበዙን አስታውቋል።
የኮሎምቢያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ፓስታራና ፣ የዛንዚባር የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኦትማን ማሱድ ኦትማንን ጨምሮ 24 ፖለቲከኞች ያለ ምንም ማብራሪያ በአንጎላ የአውሮፕላን ማረፊያ ለዘጠኝ ሰዓታት ያህል እንዲቆዩ ተደርገዋል።
ፖለቲከኞቹ ቢለቀቁም በርካቶች በረራቸው እንዳመለጣቸው 'ፕላትፎርም ፎር አፍሪካን ዴሞክራትስ (ፓድ) ገልጿል።
የአንጎላ መንግሥት ይህንንን ለማካካስ አውሮፕላን ለማቅረብ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ይህ አለመተግበሩን ፓድ አክሎ አትቷል።
"የአንጎላ መንግሥት ወደ አገሪቱ እንዳንገባ የወሰደው እርምጃ ሊገለጽ የማይችል እና ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉ የታንዛንያው ቱንዱ ሊሱ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ቢቢሲ የአንጎላን መንግሥት አስተያየት ጠይቋል።
ነገር ግን የአገሪቱ የስደተኞች እና የውጭ ዜጎች አገልግሎት (ኤስኤምኢ) ምንጭ እንደገለጹት "መባረሩ የተከሰተው በቪዛ ሂደት ውስጥ በተፈጠረው ስርዓትን ያልተከተለ አሰራር ነው። በዚህም የተነሳ ሞንድላን [የሞዛምቢክ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ]ን ጨምሮ 13 ተከታዮቻቸውን ወደ ግዛቲቷ እንዳይገቡ የተከለከሉት" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በሞዛምቢክ የተደረገው ምርጫ የተጭበረበረ ነው በሚል አገር አቀፍ የአደባባይ ተቃውሞ የጠሩት ሞንድላን በዚህ ሳምንት በአገራቸው የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ከ20 የማያንሱ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የፖለቲካ መሪዎች እና የፓርቲ ተወካዮች ወደ አንጎላ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ቱንዱ ሊሱ ገልጸዋል።
"የዚህች አገር መንግሥት አንጎላ ዲሞክራሲያዊት ናት በሚል ሽፋን የአምባገንነት ስርዓት እየገዛት ነው" ብለዋል።
ሊሱ የታንዛንያን መንግሥት በሰላ በመተቸት የሚታወቁ እና የተቃዋሚ ፓርቲ ቻዴማ መሪ ነው።
ሊሱ በአውሮፓውያኑ 2017 ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ያመለጡ ሲሆን በርካታ ዓመታትን በግዞት አሳልፈዋል።
የኬንያው ተቃዋሞ ኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንት አባል እና ሴናተር ኤድዊን ሲፉና ወደ አንጎላ እንዳይገቡ ከተከለከሉት መካከል አንዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአንጎላው ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬንኮ በአህጉሪቱ ውስጥ ራሳቸውን በአሸማጋይነት ስፍራ ስለሚያስቀምጡ ይህ ድርጊት እንግዳ መሆኑን የሞዛምቢክ የፖለቲካ ተንታኝ ቶማስ ቪየራ ማሪዮ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሎሬንኮ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሲሆኑ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭትን ሰላማዊ እልባት ለመስጠት የሚደረገውን ድርድርም በሚቀጥለው ሳምንት ያስተናግዳሉ።












