የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ነገ አስቸኳይ ጉባኤ ሊያደርግ ነው

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት በስብሰባ ላይ እጃቸውን አውጥተው

የፎቶው ባለመብት, Ashadeli Hassen

የምስሉ መግለጫ, የክልሉ ምክር ቤት የመጨረሻ ጉባኤውን ያደረገው ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ቅዳሜ መጋቢት 6/2017 ዓ.ም. አስቸኳይ ጉባኤ ለማካሄድ ጥሪ ማድረጉን ሶስት የምክር ቤቱ አባላት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ምክር ቤቱ የጉባኤውን አጀንዳ በይፋ ባይገልጽም፤ ስብሰባው የተጠራው በእስር ላይ ያሉት የምክር ቤቱ አባል አቶ ዮሃንስ ተሰማን "ያለመከሰስ መብት ለማንሳት" መሆኑን መስማታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ 2016 ዓ.ም. የተመሰረተው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የመጨረሻ ጉባኤውን ያካሄደው ባለፈው ወር ከየካቲት 9 እስከ 11/ 2017 ዓ.ም. ነበር። ለሶስት ቀናት የተካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ፤ የክልሉን ህገ መንግስት ማሻሻያ አዋጅ እንዲሁም የምክር ቤቱን መቀመጫ ወንበሮችን ብዛት ያሳደገ ሌላ አዋጅ አጽድቆ ነበር።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት ይህንን መደበኛ ጉባኤ ካካሄደ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ለአባላቱ ጥሪ ማድረጉን ሶስት የምክር ቤት አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል። አስቸኳይ ጉባኤው የሚካሄደው ቅዳሜ ጠዋት ከሁለት ሰዓት ተኩል ጀምሮ እንደሆነ እንደተገለጸላቸውም አስረድተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጉባኤው እንደሚካሄድ በስልክ ጥሪ የተገለጸላቸው ትናንት ሐሙስ እንደሆነ ገልጸዋል። ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ በዛሬው ዕለት ረፋድ አራት ሰዓት አካባቢ ተደውሎ እንደተነገራቸው ጠቅሰዋል።

እንደ ምክር ቤቱ አባልት ገለጻ፤ ጥሪው ሲተላለፍ ጉባኤ መኖሩን ከማሳወቅ ውጪ ምክር ቤቱ የሚሰበሰብበት አጀንዳ ምን እንደሆነ አልተገለጸም። ይሁንና የጉባኤው አጀንዳ በይፋ ባይገለጸም ስብሰባው የተጠራው የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት እንደሆነ መስማታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አንድ የምክር ቤት አባል "ሌላ አጀንዳ እንደሌለ እና የከለላ [የማንሳት] ጉዳይ እንደሆነ በእርግጠኝነት ሰምቻለሁ። እነማን የሚለውን ነው እርግጠኛ ያልሆንኩት" ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች መረዳታቸውን ጠቅሰዋል። ሌሎች ሁለት የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በነገው ዕለት በአጀንዳነት የሚቀርበው በእስር ላይ ያሉት የምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሃንስ ተሰማ ያለመከሰስ ከለላ እንደሆነ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ተቃዋሚውን የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ወክለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሃንስ ተሰማ በቁጥጥር ስር የዋሉት እሁድ የካቲት 30/2017 ዓ.ም. ነበር።

አቶ ዮሃንስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሌሎች ሁለት ፓርቲውን የወከሉ የምክር ቤት አባሎች ጋር በመሆን የተሻሻለው የክልሉ ህገ መንግስት እና የተወካዮች ብዛት ያሻሻሉት አዋጆች "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አቤቱታ ባቀረቡበት ሳምንት ነው።

ሶስቱ የምክር ቤት አባላት የካቲት 25 ባቀረቡት የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ፤ ከ100 ወደ 165 ያደገው የምክር ቤት መቀመጫ ብዛት ለምርጫ ክልሎች ተከፋፈለበት መንገድ "የህዝብ ብዛትን ሳይሆን ወረዳ ቁጥርን" መሰረት ያደረገ እንደሆነ በመጥቀስ ተቃውመው ነበር።

"ነባር የምርጫ ክልሎች መፍረስ እና አዲስ የምርጫ ክልሎች መመስረት" እንዲሁም ህገ መንግስቱ የተሻሻለበት ሂደትም ጥያቄ የቀረበባቸው ጉዳዮች ናቸው። የምክር ቤት አባላቱ፤ እነዚህን ለውጦች ያስተዋወቁት ሁለት አዋጆች "ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ ያልነበሩ፣ ያለተደነገጉ እንዲባሉ" እና "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባስገቡት አቤቱታ ጠይቀዋል።

ይህ አቤቱታ ለጉባኤው ከገባ ከሁለት ቀናት በኋላ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ "ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት ለማስገባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል" ያላቸውን "አንዳንድ" ቦዴፓ አመራር እና አባሎችን አስጠንቅቋል።

አቶ ዮሃንስ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Benishangul gumuzu management institute

የምስሉ መግለጫ, የምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሃንስ፤ ከሶስት ዓመት በፊት ከተሾሙበት የመንግስት ኃላፊነት በትናንትናው ዕለት ተነስተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በማህበራዊም ሆነ በሌሎች የሚዲያ አማራጮች በሚደረግ የሞቅታ ዘመቻ" የሚቀየር "አንድም ውሳኔ" እንደሌለ የክልሉ መንግስት በመግለጫው ላይ ጠቅሶ ነበር። አጀንዳዎችን በመፍጠር እና በተዛባ ሁኔታ ለሕዝብ በማድረስ" የተጠመዱ የፓርቲው አመራሮች፣ አባሎች እና ደጋፊዎችም "በአስቸኳይ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ" አሳስቧል።

ከዚህ መግለጫ ከሶስት ቀናት በኋላ አቤቱታውን ካስገቡት የምክር ቤት አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ታስረዋል። በትናንትናው ዕለት ደግሞ ተሹመውበት ከነበሩበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነት ተነስተዋል።

የክልሉ መንግስት፤ የመንግስት ኃላፊነት ከሰጣቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ዮሃንስ፤ ተቋሙን ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከሶስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ መርተዋል። አቶ ዮሃንስ ከታሰሩ በኋላ ተቋሙን የመምራት ኃላፊነትን ሲወጡ የቆዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አበበ እንድረስ እንደሆኑ የተቋሙ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትናትናው ዕለትም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ በእስር ላይ ያሉትን አቶ ዮሃንስን ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነት ማንሳታቸውን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

በምትኩም እስከ ትናንት ድረስ የክልሉን የሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ አብዱልሰላም ኢብራሂም እንደተሾሙ ተገልጿል።

የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር እና የምክር ቤት አባል አቶ ዮሃንስ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ዮሃንስ ወደ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት የምክር ቤት አባል በመሆናቸው ያገኙት ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መያዛቸውን በመጥቀስ "ለመርማሪ ፖሊሶች ቃል ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሆን እንደሚችልም" ተናግረዋል።

ሁለት የምክር ቤት አባላት፤ "የአቶ ዮሃንስ ያለመከሰስ መብት ለማንሳት" አስቸኳይ ጉባኤ የተጠራው የምክር ቤት አባሉን "ፍርድ ቤት ለማቅረብ እንዲቻል ነው" የሚል ግምት እንዳላቸው አስረድተዋል።

ቢቢሲ፤ ለነገ የተጠራውን ጉባኤ በተመለከተ ከክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።