በስዊዲን የተፈጸመው ቁርአንን የማቃጠል ድርጊት በሙስሊም አገራት ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
ሲዊዲን ውስጥ አንድ ግለሰብ ተቃውሞውን ለመግለጽ የፈጸመው ቅዱስ ቁራአንን የማቃጠል ድርጊትን በርካታ ሙስሊም አገራት ተቃወሙት።
ስዊዲን ውስጥ ይኖራል የተባለው ኢራቃዊ ሳልዋን ሞሚካ የቅዱስ ቁርአን ገጾችን ያቃጠለው ረቡዕ ዕለት በዋና ከተማዋ ስቶክሆልም ውስጥ በሚገኘው መስጂድ ፊት ለፊት ነው።
ይህንንም ተከትሎ ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያን እና ግብፅን ጨምሮ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ድርጊቱን በጽኑ አውግዘውታል።
በተጨማሪም የኔቶ አባል እና ሲዊዲን በጦር ማኅበሩ ውስጥ ለመግባት ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ድምጽ የመስጠት ሥልጣን ያላት ቱርክ ክስተቱን “አስቀያሚ ድርጊት” በማለት ተቃውማዋለች።
ቱርክ ጨምራም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ “ይህን የመሰለ ፀረ እስልምና ድርጊት ተቀባይነት የለመውም” በማለት ቁጣዋን ገልጸለች።
በሙስሊሞች ዘንድ ቁርአን የፈጣሪን ቅዱስ ቃልን የያዘ መጽሐፍ ተደርጎ ስለሚታመን፣ ሆን ተብሎ በመጽሐፉ ላይ የሚፈጸም ጥፋት ወይም አከብሮትን መንፈግ በቀላሉ የሚታይ ጥፋት ተደርጎ አይታይም።
ስዊዲን ውስጥ ረቡዕ ዕለት ቅዱስ ቀርአን የተቃጠለበት ክስተት ያጋጠመው፣ በሙስሊሞች የጊዜ ቀመር ዋነኛ ከሚባሉት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የኢድ አል አድሃ በዓል በመላው ዓለም በሚከበርበት ቀን ነው።
ቅዱስ ቁርአንን ያቃጠለው ግለሰብ በመናገር ነጻነት ሕግ መሠረት ተቃውሞውን እንዲያሰማ ከፖሊስ ፈቃድ ማግኘቱ የተነገረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ጥላቻን በመቀስቀስ ድርጊት ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ይህ የተቃውሞ ድርጊት በሌሎች አገራት ውስጥ ቁጣን ቀስቅሷል።
ሞሮኮ በስቶክሆልም ያሏትን አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የጠራች ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ራባት ያሉትን የስዊዲን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚን ጠርታ አናግራለች።
ኢራቅ በበኩሏ ድረጊቱ “ሐሳብን ከመግለጽ ነጻነት ጋር የሚገናኝ ሳይሆን፣ ጥላቻን መሠረት ካደረገ ጸብ ጫሪ መንፈስ የመነጨ ነው” በማለት ተቃውማዋለች።
ኢራን በበኩሏ የኢራቅን ተቃውሞ በማስተጋባት ቅዱስ ቁርአንን የማቃጠሉ ድርጊት “ተቀባይነት የሌለው እና ጸብ አጫሪነት ነው” ስተለው፣ ግብፅ ደግሞ ድርጊቱን “አሳፋሪ” በማለት በተለይ ደግሞ ሙስሊሞች ኢድ አል አድሃን በሚያከብሩበት ጊዜ መፈጸሙ ጸብ አጫሪነት ነው ብላለች።
በዚህ ሳምንት በመካሄድ ላይ ባለው የሐጂ ጉዞ ላይ የሚሳተፉ 1.8 ሚሊዮን ሙስሊም ምዕመናን እያስተናገደች ያለችው ሳዑዲ አረቢያ “እንዲህ አይነቱ ተደጋጋሚ የጥላቻ ድርጊት በምንም አይነት ማሳመኛ ተቀባይነት የለውም” ስትል ተቃውሞዋን ገልጻለች።
የስዊዲን ጠቅላይ ሚኒስትር ኦልፍ ክሪስተርሰን ክስተቱን አስመልክቶ እንደተናገሩት፣ ቁርአንን ማቃጠል “ሕጋዊ ቢሆንም ተገቢ ግን አይደለም” ብለዋል።
ወራት በፊት ስዊዲን ውስጥ በተመሳሳይ በተቃውሞ ቁርአንን ለማቃጠል ተይዞ የነበረ ዕቅድ ብጥብጥን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።
በቅርቡ ተመሳሳይ ተቃውሞን ለመግለጽ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ፖሊስ ያልተቀባለቸው ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ግን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መሠረት አድርጎ እንዲፈቀድ ውሳኔ አሳልፏል።












