አፍሪካውያን ያለ ቪዛ ወደ ጋና መግባት እንደሚችሉ ተገለጸ

ፓስፖርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ አገራት ፓስፖርት የያዙ ሁሉ ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ጋናን መጎብኘት እንደሚችሉ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ተናገሩ።

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ይህንን እቅዳቸውን ባለፈው ወር አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን አርብ ዕለት ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው ላይ ፖሊሲው ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

አንዲት አፍሪካን የሚያቀነቅኑ ግለሰቦች በአህጉሪቱ ከቪዛ ነጻ የሆነ ጉዞ እንዲኖር ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ምኞት የነበራቸው ሲሆን፣ ውሳኔው ለምጣኔ ኃብት ትብብር አስፈላጊ ነው ተብሎ ይታሰባል።

ጋና አሁን ከአህጉሪቱ የተለያየ ክፍል ለሚመጡ መንገደኞች ከቪዛ ነጻ የሆነ አሰራርን በመዘርጋት አምስተኛዋ አፍሪካዊት አገር ሆናለች።

ከዚህ ቀደም ሩዋንዳ፣ ሲሸልስ፣ ጋምቢያ እና ቤኒን አፍሪካውያን ያለምንም ቪዛ አገራቸውን መጎብኘት እንደሚችሉ አስታውቀው ነበር።

ለስምንት ዓመት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝዳንት አኩፎ-አዶ ለፓርላማ ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው "ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ሁሉም የአፍሪካ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ወደ ጋና ከቪዛ ነጻ እንዲገቡ የሚያስችለውን መመርያ በማፅደቄ ኩራት ይሰማኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት ተግባራዊ የሆነውን የነጻ ንግድ ቀጠና ውሳኔን በማጣቀስም "ይህ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና እና በዓለም ላይ ትልቁ የንግድ አጋር ቀጣይ እርምጃ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ጋና ለ26 የአፍሪካ አገራት ዜጎች ከቪዛ ነፃ የጉዞ እድል በመስጠት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ነበር።

ጋና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአህጉሪቱ የሚመጡ እና ለአፍሪካ ዲያስፖራዎች የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን እየሰራች ነው።

እ.ኤ.አ. በ 2019 አኩፎ አዶ "የመመለስ ዓመት" በሚል አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸው በአገራቸው ሀብታቸውን አንዲያፈስሱ የሚያስችል ዘመቻ አስጀምረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን ከማስረከባቸው በፊት ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው የሰሯቸውን ሥራዎች መለስ ብለው ቃኝተዋል።

ምንም እንኳን አብዛኛው ጋናዊ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታን ቢያሳልፍም ፣ "እድገቱ ወደ ቅድመ-ኮቪድ ዘመን ተመልሷል" ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም "እያደገች ያለች" አገርን አስረክቤያለሁ ብለዋል።

ለሁለት የምርጫ ዘመን ያገለገሉት አኩፎ አዶ ባለፈው ወር ለድጋሚ ምርጫ መወዳደር አልቻሉም። ነገር ግን ፓርቲያቸው እርሳቸውን ለመተካት የመረጣቸው ግለሰብ፣ ምክትል ፕሬዝደንት ማሃሙዱ ባውሚያ፣ በጆን ማሃማ በከፍተኛ ልዩነት ተሸንፈዋል።

ማሃማ ማክሰኞ ዕለት ቃለ መሃላ በመፈጸም የአገሪቱን ርዕሰ ብሔርነት በይፋ ይረከባሉ።