ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ እና የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሞሃመድ ኑር

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ እና የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሞሃመድ ኑር

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የሚመራ የአገሪቱ ከፍተኛ ልዑካን ወደ ሶማሊያ ታህሳስ 24/ 2017 ዓ.ም ማቅናቱን ተከትሎ ነው አገራቱ በአውሶም ተልዕኮ ለመተባበር ስምምነት ላይ ደርሰዋል የተባሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ነሐሴ 25/ 2017 ዓ.ም ያወጣው መግለጫ በደፈናው አገራቱ በተልዕኮው ላይ በጋራ ይሰራሉ ቢልም የኢትዮጵያ ወታደሮች በመጪው ጥር በሚሰማራው የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ ስለ መሳተፋቸው ያለው ነገር የለም።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታን ጠቅሶ ብሉምበርግ ባወጣው ዘገባ የመከላከያ ሚኒስትሯ ወደ ሶማሊያ ያቀኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ውይይት ለማድረግ ነው ብሏል።

ሚኒስትር ዴዔታው "በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአውሶም ለማካተት እያሰበች ነው" ማለታቸውንም ዘገባው አክሏል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያን ወታደሮች በአውሶም ውስጥ ላለማካተት አስተላልፋ የነበረውን ውሳኔ ለመቀልበስ ማሰቧንም የብሉምበርግ ዘገባ ያትታል።

ኢትዮጵያ በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች ጦሯ በአውሶም ተልዕኮ እንደማይሰማሩ የሶማሊያ ባልስልጣናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አውሶም የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ)ን እንዲተካ ያሳለፈውን ውሳኔ በቅርቡ ማጽደቁ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በውሳኔው መሰረት የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እስከ መጪው የአውሮፓውያኑ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 1,040 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ እስከ 12 ሺህ ገደማ መለዮ ለባሽ የጸጥታ አካላት በአዲሱ ተልዕኮ (አውሶም) እንዲያሰማሩ ፈቅዷል።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ውጥረት ያረበገውን የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ ልዑካን ወደ ሶማሊያ ያቀኑት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ያቀደ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ያደረጉት ውይይት ገንቢ እንደነበር ገልጸው በሶማሊያ እና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የተገለጸበት ነበር ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ "ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ያላቸውን ውዝግብ መፍታታቸውን" የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ አህመድ ሙዓሊም ፊቂ መግለጻቸውን ቢቢሲ ሶማሊ ዘግቧል

ሚኒስትሩ በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባ የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ ተቋጭቷል ማለታቸውን የሶማሊ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ መዘገቡን ቢቢሲ ሶማሊ አስነብቧል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ባለፈው አመት ያስገኘውን ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህ ውጥረት መቋጫ ያገኘው "በሶማሊያ ብልሃት እና ጽናት ነው" ብለዋል

"አለመግባባቱ ተፈትቷል። አለመግባባቱ የተፈታው ጥያቄያችንን ወይም መርሆዋችንን ወደ ጎን በማድረግ እና ገሸሽ በማድረግ ሳይሆን የሶማሊያ ጥያቄ ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው" ብለዋል።

ሚኒስትሩ "የአንድን አገር መሬት ወይም ባህር የፈለግነው እኛ አይደለንም" ቢሉም ውዝግቡን በውይይት መፍታት የበሰለ አካሄድ ነው ብለዋል።

የባህር በር ውይይቶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር ውይይት መደረግ የለበትም የሚሉ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው ይህንን አጣጥለውታል። "በዲፕሎማሲ አይሆንም የሚባል ነገር የለም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ልዑካን

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሶማሊያ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ስላገኘ ውዝግቡ እልባት ማግኘቱን በጠቀሱበት በዚህ ንግግራቸው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባቸውን የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ሰርዛ እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባህር በር መግባቢያ ስምምነት በተመለከተ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን አለመግባባት በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ከሁለቱ አገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከፈረመች በኋላ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሰረት፤ "ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።"

ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ "የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ" ሲል ያትታል።

በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የያዘው ነጻነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ መንግሥት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ መካከል ቱርክ ውስጥ የተደረሰውን ስምምነት በሚመለከት ሶማሊላንድ ሌላ አገር በመሆኗ ይህ ጉዳይ የሚመለከታት እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል።

አዲሱ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ሞሐመድ ፋራህ አብዲ "የፈረሙት ሁለቱ አገራት ናቸው፣ እኛ ሶማሊላንድ ነን። ሁለቱ ወንድማማች አገራት የራሳቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት። እነሱ ተነጋግረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተለመደ ነገር ነው። እኛን የሚመለከት አይደለም" ሲሉ መናገራቸው ቢቢሲ ሶማሊ ዘግቧል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በሶማሊላንድ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ ያለበትን ሁኔታን በተመለከተ ሲናገሩ አዲሱ መንግሥት ገና ሥልጣን መረከቡ በመሆኑ ጊዜ ወስዶ እንደሚመለከተው እና የሚወስንበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውጪ መሆኑን በይፋ አስታውቀው ነበር።

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርታ ኢትዮጵያ ሰራዊቷን አሰማርታ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።

በአሁኑ ጊዜ ቆይታው ለተጠናቀቀው አትሚስ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ ወታደሮቻቸውን ማዋጣታቸው የሚታወስ ሲሆን ለቀጣዪ ተልዕኮ አውሶም የሚሰማሩ ወታደሮች ከየትኛው አገር እንደሚሆኑ የመምረጥ ኃላፊነቱ የሶማሊያ ይሆናል።