በአዋሽ ፈንታሌ "እሳተ ጎመራ" መከሰቱ ተሰማ

አዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው እሳተ ጎመራ

የፎቶው ባለመብት, SULTAN KAMIL

ከሰሞኑ በርካታ የመሬት መንቀጥቀጦች ሲያስተናግድ በነበረው አዋሽ ፈንታሌ እሳተ ጎመራ መከሰቱን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ተቋም አስታውቋል።

ተቋሙ በፌስቡክ ገፁ ያጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ከአካባቢው ጭስ ከመሬት ፈንቅሎ ሲወጣ ያሳያል።

እሳተ ጎመራው በአዋሽ ፈንታሌ ዶፋን የሚባል ተራራ ላይ መከሰቱንም ተቋሙ አስታውቋል።

አዋሽ ፈንታሌ ባለፉት ሳምንት በተደጋጋሚ በርካታ የመሬት መንቀጥቀጦች ሲያስተናግድ ቆይቷል።

እሳተ ጎመራውን ተከትሎ በአካካቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የአፋር ክልል ባለሥልጣን ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ እንደሚሉት በሥፍራው የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እየገቡ ነው።

በተጨማሪ ከአካባቢው ተንቃሳቃሽ ምስል የላኩ ነዋሪዎች ሥፍራውን ለቀው እየወጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ እሳተ ጎመራ የተከሰተው አርብ ዕለት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ክስተቱን "እሳተ ጎመራ" ብሎ ለመጥራት ጊዜው ገና ነው ብለዋል ሲል ሮይተርስ አስነብቧል።

አንዳንድ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እየወጡ ነው። እኛ በተቀናጀ መንገድ ነዋሪዎችን ከሥፍራው ለማሸሽ እየሞከርን ነው" ሲሉ ኮሚሽነሩ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በአካካቢው አሁንም የመሬት መንቀጥቀጡ እንደቀጠለ የሚናገሩት ባለሥልጣናት ንዝረቱ ከፍ ያለ መሆኑን አሳውቀዋል።

አሁናዊ የመሬት መንቀጥቀጥ መረጃዎችን የሚያቀርበው የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የጂኦሎጂ ሰርቬይ ድረ-ገፅ ሐሙስ ለሊት በአዋሽ ፈንታሌ፣ መተሐራ እና በደብረ ሲና አካባቢ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች እንደነበሩ ጠቁሟል።

ቮልኬኖ ዲስከቨሪ የተባለው ድረ-ገፅ ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ያገኘውን ተንቀሳቃሽ ምስል ዋቢ አድርጎ ዶፋን ተራራ አካባቢ ጋዝ፣ ድንጋይ እና ጭቃ የተፋ እሳተ ጎመራ እንደነበር ዘግቧል።

ሥፍራው ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚሰከትበት ቦታ መሆኑን አስታውቆ ምናልባት ተጨማሪ እሳተ ጎመራ ሊከሰት እንደሚችል ጠቋሚ ነው ብሏል።

ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 21/2017 በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ በአንድ ቀን 10 የመሬት መንቀጥቀጦች መመዝገባቸው ይታወሳል።

በአገሪቱ ከ2017 አዲስ ዓመት ጀምሮ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች እየተደገጋገሙ እና ንዝረታቸውም እስከ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ድረስ እየተሰማ ይገኛል።

የዘርፉ ባለሞያዎች በተለይም ወርሃ መስከረም እና ጥቅምት ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች የነበሩባቸው ወራቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

በኅዳር ወር ጋብ ብሎ የነበረው ርዕደ መሬት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ሲሆን፤ ከእስካሁኑ በሬክተር ስኬል ከፍተኛው ርዕደ መሬት የታየውም ባለፉት ቀናት ነው።

የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል?

መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንብርብሮች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል 'ኮር' ይባላል። ቀጥሎ የሚገኘው 'ማንትል' ነው። በመቀጠል 'ክረስት' ይመጣል። ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው።

ክረስት እና የማንትል የላይኛው አካል ቴክቶኒክ ፕሌትስ ከተባለው ድንጋይ የተሠሩ ናቸው።

'ቴክቶኒክ ፕሌትስ' ዝግ ባለ መልኩ ሁሌም ይጓዛሉ። በዚህ መካከል ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ ሆኖ በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን የሚነቀንቀው እና የሚያፈራርሰው።

በቀላል አገላለጽ በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ መሬት ትንቀጠቀጣለች ማለት ነው።

'ቴክቶኒክ ፕሌትስ' በየዓመቱ በጥቂት ሴንቲ ሜትሮች እንቀስቃሴ ያደርጋሉ። እነዚህ መሬት የተዋቀረችባቸው አለቶች በተለያየ አቅጣጫ ነው የሚንቀሳቀሱት። ፍጥነታቸውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ አለቶች እርስ በርስ ተፋፍገው ሊያልፉ ይችላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ክፍል ከሌላኛው እየራቀ ሊሄድ ይችላል። እርስ በርስም የሚጋጩ አሉ።

በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ድንጋዮች ሲተፋፈጉ ርዕደ መሬት ያስከትላሉ። በመተፋፈጉ መካከል የሚከሰተው ኃይል ከፍተኛ ስለሆነ የመሬት ማዕበል ይፈጥራል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የባሕር ጠለል ላይ ሲከሰት ደግሞ ከፍተኛ ማዕበል ይፈጠራል። ሱናሚ የሚባለውም ይህ ነው።

በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በተለየ ቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው።

ይህ የመሬት ውስጥ ንቅናቄ እና መንቀጥቀጥ ጥንካሬ የሚለካበት መሳሪያ ሬክተር ስኬል ይባላል። ይህ መለኪያ ርዕደ መሬቱ የፈጠረውን ማግኒቲዩድ ይመዝናል።