ፍሪጅ ውስጥ ውሾች፣ ድመቶች እና እባቦች ያስቀመጠው አሜሪካዊ ታሰረ

ግለሰቡ እንስሳት ላይ ባሳየው ጭካኔ 94 ክሶች እንደቀረቡበት ተሰምቷል።

የፎቶው ባለመብት, MOHAVE COUNTY SHERIFF'S OFFICE

የምስሉ መግለጫ, ግለሰቡ እንስሳት ላይ ባሳየው ጭካኔ 94 ክሶች እንደቀረቡበት ተሰምቷል።

በአሜሪካ በአሪዞና ግዛት አንድ ግለሰብ ማቀዝቀዣው ውስጥ ውሾች፣ ድመቶች እና ወፎችን ጨምሮ 183 እንስሳት መገኘቱን ተከትሎ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

ማይክል ፓትሪክ ቱርላንድ የተባለው የ43 ዓመቱ ሰው የተወሰኑ እንስሳትን በሕይወት እያሉ ፍሪጅ ውስጥ መክተቱን ለሕግ አስከባሪ አካላት አምኗል።

ግለሰቡ እንስሳት ላይ ባሳየው ጭካኔ 94 ክሶች እንደቀረቡበትም ተሰምቷል።

የሕግ አስከባሪ ጽሕፈት ቤቱ ቃል አቀባይ አኒታ ሞርቴንሰን በቦታው የተነሱ ምስሎች "ፍፁም አስጸያፊ እና ልብ ሰባሪ ነበሩ" ሲሉ ተናግረዋል።

"እንስሳን እንደሚወድ ሰው ምስሎቹን እያየሁ እያለቀስኩ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ፎቶግራፎቹን ለሌሎች ለማጋራት እጅግ አሰቃቂ ናቸው ብለዋል።

የግለሰቡ ባለቤትም እየተፈለገች እንደሆነ ተነግሯል።

ፖሊስ ከአንዲት ሴት በደረሰው ጥቆማ መሠረት ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ያዋለው ሲሆን ጥቆማውን የሰጠችው ሰው ከጥቂት ወራት በፊት እሱ ጋር የሚራቡ እባቦችን ትታ ሄዳ እንደነበር ገልጻለች።

ሆኖም ግለሰቡ ከአከባቢው እንደተሰወረ እና እባቦቿን መልሳ ማግኘት እንዳልቻለች ለፖሊስ አስረድታለች።

ቱርላንድ እና ባለቤቱ ከሚኖሩበት ቤታቸው ከወጡ በኋላ የቤቱ ባለቤቶች እንደደወሉላት እና ባለቤቱ ቤቱን ለማጽዳት ሲመጣ ፍሪጁ የሷን እባብ ጨምሮ በበርካታ እንስሳት ተሞልቶ መገኘቱንም ጨምራ ተናግራለች።

ሕግ አስከባሪዎቹ በበረዶ ከደረቁ እንስሳት መካከል ውሾች፣ ኤሊዎች፣ እንሽላሊቶች፣ ወፎች፣ እባቦች፣ አይጦችና ጥንቸሎች መገኘታቸውን አሳውቀዋል።

ከአስር ቀናት በኋላ ቱርላንድ ወደ ቤቱ እንደተመለሰ ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውለውታል። ግለሰቡ እንስሳቱን ለማቀዝቀዝ ያነሳሳው ነገር ምን እንደሆነ ግን እስካሁን አልታወቀም።