በአሜሪካ የስምንት ዓመቷን ታዳጊ የገደሉት ሦስት ፖሊሶች ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, BRUCE L CASTOR JR
በአሜሪካ የስምንት ዓመቷን ታዳጊ ፋንታ ቢሊቲ ተኩሰው የገደሉት ሦስት ፖሊሶች ክስ ተመሠረተባቸው።
አምና ነሐሴ ላይ ፖሊሶቹ በፊላደልፊያ ከተማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ተኩስ ከተሰማ በኋላ ወደ ቦታው አቅንተው ነበር።
ትምህርት ቤቱ ውስጥ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ እየተካሄደ የነበረ ሲሆን፤ ፖሊሶቹ ከትምህርት ቤቱ ውጭ ተኩስ ከፍተዋል።
መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች አሉበት ብለው በጠረጠሩት መኪና ላይ ተኩስ ሲከፍቱ መኪና ውስጥ የነበረችው ታዳጊዋ ፋንታ ቢሊቲ ነበረች።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በዚያን እለት ሁለት ወጣቶች እርስ በእርስ እየተታኮሱ ነበር። ፖሊሶች በቦታው ደርሰው ተኩስ ከከፈቱ በኋላ ግን የታዳጊዋ ሕይወት ተቀጥፏል።
እርስ በእርስ ይታኮሱ የነበሩት ወጣቶች ጥቅምት ላይ በመጀመሪያ ደረጃ ግድያ ተከሰው የነበረ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ አሁን ክሱን አንስቷል።
የ16 እና የ18 ዓመት ወጣቶቹ ለታዳጊዋ ሞት ምክንያት የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ነበር ተከሰው የነበረው።
የወጣቶቹ ክስ ከተቋረጠ በኋላ ፖሊሶቹ ዴቨን ስሚዝ፣ ሻን ፓትሪክዶላን እና ብራየን ጄምስ ዴቫንሊ ነፍስ በማጥፋት እና በችልተኝነት ክስ ተከፍቶባቸዋል።
በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ጥበቃ ላይ የነበሩት ፖሊሶቹ ተኩስ የሰሙት እነሱ ከነበሩበት ቦታ በ42 ሜትር ርቀት ላይ ነው።
አንድ መኪና እነሱ ወደነበሩበት ሲጓዝ መኪናው ላይ 25 ጊዜ ተኩሰዋል። በተኩሱ የፋንታ የ12 ዓመት እህትና እናትን ጨምሮ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ፋንታ ወዲያው ሕይወቷ አልፏል።
የዳላዌር ግዛት ዐቃቤ ሕግ ጃክ ስቶስቲመር ለሲቢኤስ ኒውስ "ፖሊሶቹ ፋንታ እንደገደሏትና ሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳደረሱ አረጋግጠናል" ብለዋል።
"ተኩስ የከፈቱት ኢላማ ባልነበሩ ሰዎች ላይ ነው። የተኮሱት ወደተሳሳተ አቅጣጫ ነው። የተኮሱት በተሰበሱ ሰዎች ላይ ስለሆነ ተጠያቂ መደረግ ይገባቸዋል።" ሲሉም አክለዋል።
የፋንታ ቤተሰብ ጠበቃ እንዳሉት፤ ታዳጊዋ ብሩሕ አእምሮ ያላት ደስተኛ ልጅ ነበረች። "ማንም ሰው እሷን በማየቱ ብቻ ደስ ይለው ነበር። ሕይወቷ እንዲህ መቀጠፉ እጅጉን ያሳዝናል" ብለዋል።
የፖሊሶቹ ጠበቆች በበኩላቸው "ደንበኞቻችን ንጹህ ናቸው። በተፈጠረው ነገር ሳቢያ የደረሰው ሐዘን ልባቸውን ሰብሮታል" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
"የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የወንጀል አውድማ ባደረጉ ታጣቂ ወንጀለኞች ሳቢያ የደረሰ አሳዛኝ ክስተት ነው። ይህ ክስተት ለንጹህ ልጅ ሞትና ለሦስት ሰዎች ጉዳት ምክንያት ሆኗል" ሲሉም ጠበቆቹ አክለዋል።












