የአውሮፓ አቪየሽን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ዳግም መብረር እንዲችል ፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ የአቪየሽን ደኅንነት ኤጀንሲ (EASA ) የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከዚህ በኋላ ወደ ሰማይ ለመመለስ ዝግጁ ናቸው ሲል አረጋገጠ።
የኤጀንሰው ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አውሮፕላኖቹ ከዚህ በኋላ ለመብረር አንዳችም ስጋት እንደሌለባቸው እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን ብለዋል።
የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓትሪክ፣ ድርጅታቸው ከአውሮፕላኖቹ አምራች ጋር በመሆን ጥብቅ ፍተሻና ምርመራ እንዳደረገና ለበረራ ዝግጁ እንደሆኑም እንዳረጋገጠ ለቢቢሲ አብራርተዋል።
አውሮፕላኖቹ ከበረራ የተገለሉት በአወሮፓውያኑ 2019 እንደነበር ይታወሳል።
አውሮፕላኖቹ ከበረራ የታገዱት በኢትዯጵያና በኢንዶኔዢያ ሰማይ ላይ ተከስክሰው 346 መንገደኞች ማለቃቸውን ተከትሎ ነበር።
አሁን የቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች በአሜሪካ እና በብራዚል፣ ከጥር አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በመላው አውሮፓ በረራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
የማክስ አውሮፕላኖች የመጀመርያው አደጋ የተመዘገበው በላየን አየር መንገድ ሲሆን ይህም በጥቅምት 2018 በኢንዶኒዢያ ሰማይ ላይ ነበር።
ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ወደ ናይሮቢ በማቅናት ላይ በነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እንደነበር ይታወሳል።
የሁለቱም አደጋዎች ምንጭ ከአውሮፕላኑ የአደጋ ጊዜ ሶፍት ዌር እንከን ጋር የተያያዘ እንደነበር አይዘነጋም።
ሶፍትዌሩ ራሱን በራሱ የሚያዝና፣ በተሳሳተ ጊዜ ራሱን የሚያነቃ ሆኖ የተሰራ ሲሆን፣ አውሮፕላኑን ከአብራሪው ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን የሚያደርግ ሆኖ በመነደፉ እክል እንደነበረበረበት በኋላ ላይ ተረጋግጧል።
የአውሮፓ አቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እነዚህ እክል የነበረባቸው አውሮፕላኖች ወደ ሰማይ እንዲመለሱ ለመወሰን የነበረባቸው እክል ብቻ መመርመር በቂ አልነበረም። ስለዚህ መላ ስሪታቸውን እንደ አዲስ ፈትሸን ነው እንዲመለሱ የወሰነው ብለዋል።
ለማክስ አውሮፕላን የተገጠመለት አዲስ ሶፍትዌርን በተመለከተ አብራሪዎች አዲስ ስልጠና እንዲወስዱ ይገደዳሉ ተብሏል።
















