ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በቅርቡ በረራ ሊጀምር ነው

ቦይንግ 878

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

ቦይንግ የተሰኘው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ 737 ማክስ በጎርጎሮሳውያኑ አዲስ ዓመት ወደ በረራ እንደሚመለስ አሳውቋል።

737 ማክስ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተሰከቱ ሁለት አደጋዎች በኋላ ሰማይ ላይ እንዳይታይ እግድ ተጥሎበት ይገኛል።

የአንዶኔዥያው ላየን ኤይር ንብረት የሆነው ማክስ 737 ተከስክሶ አሳፍሯቸው የነበራቸው 189 ሰዎች ማለቃቸው ይታወሳል። አደጋው በተከሰተበት ወቅት የኢንዶኔዥያ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋው አውሮፕላኑ ላይ በነበረ እክል ምክንያት ነው የተከሰተው ቢሉም ድርጅቱ እጄ የለበትም ማለቱ ይታወሳል።

ድርጅቱ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ወደ ሰማይ እንዲመለስ ከፈቃድ ሰጭ አካላት ጋር በቅርብ እየሠራሁ ነው ብሏል። አስፈላጊውን ሥልጠና አዘጋጅቻለሁ የሚለው ቦይንግ ቀጣይ የጎርጎርያውን አዲስ ዓመት [2020] ከመግባቱ በፊት 737 ማክስ በረራ ሊጀምር እንደሚችል እምነት አለኝ ይላል።

ባፈለው ዓመት ጥቅምት ነበር የላየን ኤይር ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የተከሰከሰው። የአደጋውን ምክንያት ሲመረምሩ የነበሩ ግሰለቦች መካኒካዊ እና የዲዛይን ችግሮች ከበረራ መቆጣጠሪያው ጋር ተደባልቀው ነው አደጋው የተከሰተው ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

አደጋ መርማሪዎቹ አውሮፕላኑ ወደ ላይ ቀና እንዲል ወይም አፍንጫውን እንዲደፋ የሚያደርገውን ክስተት ለማስተካከል ተብሎ ቦይንግ የገጠመው ሥርዓት ነው ለአደጋው ምክንያት የሆነው ይላሉ።

የላየን ኤይር አደጋ ሙሉ ዘገባ አርብ ዕለት ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን የአደጋው ተጠቂ ቤተሰቦች ስለ አደጋው ዝርዝር መረጃ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።

ቦይንግ 737 ማክስ ከኢንዶኔዥያው አደጋ በኋላም ጥቅም ላይ እየዋለ ነበር። ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላ ተመሳሳይ ባሕርይ ያለው አደጋ የኢትዮጵያ ንብረት በሆነ አውሮፕላን ላይ ደረሰ። ከዚህ አደጋ በኋላ ነው አውሮፕላኑ አገልግሎት እንዳይሰጥ የታገደው።

የቦይንግ ነገር ገና ሳይበርድ ነው ታድያ የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኬቪን ማክአሊስተር ከመንበራቸው የተነሱት። ማክአሊስተር የቦይንግ የንግድ አውሮፕላኖች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ቦይንግ በ737 ማክስ አውሮፕላን ሳቢያ ትርፌ በግማሽ ቀንሷል ሲል ተደምጧል። አልፎም የ787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ምርቱን በግማሽ ለመቀነስ ወስኗል።

የቢቢሲው ተንታኝ ቶም ባሪጅ ቦይንግ 737 ማክስ በቅርቡ በአሜሪካ ሰማይ ላይ ይታያል ብሎ መገመት ከባድ ነው ይላል። አሜሪካውያን ፈቃድ ሰጭዎች ይሁን ቢሉ እንኳ የአውሮጳ ተቆጣጣሪዎች በቀላሉ ፈቃድ ይሰጣሉ ማለት ዘበት ነው ሲል ይተነትናል።