ቦይንግ፡ አደጋ የደረሰበት ማክስ 737 አውሮፕላን የሙከራ በረራ ሊጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, BOEING
የአውሮፓ ኅብረት አቪየሽን ኤጀንሲ እክል ገጥሟቸው ዘለግ ላለ ጊዜ ከሥራ ውጭ ሆነው የቆዩትን የቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖችን በድጋሚ የሚሞክርበትን የጊዜ ሰሌዳ አወጣ።
የአውሮፓ ኅብረት የአቪየሽን ደኅንነት ኤጀንሲ እንደተናገረው በማክስ 737 አውሮፕላኖች ሙከራዎቹ የሚካሄዱት ከመስከረም 7 ጀምሮ በካናዳ ቫንኩቨር ይሆናል።
በቦይንግ የአውሮፕላን ሽያጭ ታሪክ ተወዳጅና ብዙ ገበያ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው የቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖች አንዳች ቴክኒካዊ እክል አለባቸው ተብለው ከገበያ እንዲወጡ የሆኑት ባለፈው ዓመት በተለያዩ አገራት ተከስክሰው ለ346 ሰዎች ሞት ምክንያት ከሆኑ በኋላ ነው።
የአውሮፓ አቪየሽን አውሮፕላኖቹን ለመሞከር የወሰነው የአሜሪካ አቪየሽን ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ መድረሱን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ አቪየሽን ተቆጣጣሪ ከሁለት ወራት በፊት ይህንኑ ሂደት መጀመሩ ይታወሳል።
ሆኖም የአውሮፓ አቻው እንዳስታወቀው የአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር አውሮፕላኖቹ ችግር የለባቸውም ብሎ እውቅና ስለሰጣቸው ብቻ አውሮፓ ውስጥ መብረር ይችላሉ ማለት አይደለም።
የአውሮፓ አቪየሽን ጨምሮ እንዳስታወሰው አሁን ሳይሆን ቀደም ብሎም ቢሆን ለረዥም ጊዜ ከቦይንግና ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ማክስ 737 ወደ አየር በሚመለስበት ሁኔታ አብሮ እየሰራ ነበር።
ነገር ግን ከብዙ ሂደት በኋላ በመጨረሻ አሁን ነው የሙከራ በረራ ቢደረግ አደጋ እንደሌለው ኩባንያው ማሳመን የቻለው።
የሙከራ በረራው ቀደም ብሎ ሊካሄድ ይችል እንደነበረ ያስታወቀው አቪየሽኑ የኮቪድ-19 መከሰትና በአውሮፓና አሜሪካ የበረራ ግንኙነት መስተጓጎል የሙከራ ጊዜውን ለመግፋት እንዳስገደደው አስታውቋል።
ኤጀንሲው በቫንኩቨር ብቻ ሳይሆን ከመስከረም አንድ ጀምሮ ደግሞ በለንደን ጋትዊክ አየር መንገድም ተመሳሳይ የበረራ ሙከራ ለማድረግ እቅድ ይዟል።
ይህ በእንዲህ እዳለ የአሜሪካ የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ማክስ 737 አውሮፕላንን ዳግም ወደ አየር ለመመለስ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።
ከእነዚህ መካከል የበረራ ቁጥጥር ሶፍትዌርን ማሻሻልና ሌሎች ዘርዘር ያሉ ውስብስብ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን አስቀምጧል።
ቦይንግ በሚቀጥለው የፈረንጆት ዓመት መጀመሪያ በነበረባቸው እክል ተሳፋሪዎቻቸውን ለሞት የዳረጉት የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ወደ በረራ እንደሚመለሱ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው።
የአቪየሽን ባለሥልጣናት እነዚህን ተመራጭ የአውሮፕላን ምርቶች ከበረራ ያገዳቸው በላየን አየር መንገድና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በአምስት ወራት ልዩነት አሰቃቂ አደጋ ማድረሳቸውን ተከትሎ ነበር።
በሁለቱ አደጋዎች በድምሩ 346 ተሳፋሪዎች መሞታቸው አይዘነጋም።
አውሮፕላኖቹ ከበረራ ይታገዱ የሚለው ውሳኔ 103 ዓመት ዕድሜ ባስቆጠረው የአሜሪካ ግዙፉ ኩባንያ ቦይንግ ላይ አጋጥሞት የማያውቅ ትልቅ ኪሳራ አምጥቶበታል ተብሏል።
ኪሳራው የመጣው በርካታ አየር መንገዶች አውሮፕላኖቻቸውን በማቆማቸው፣ ቀብድ የከፈሉትን በማስመለሳቸው፣ በርካታ ትዕዛዞችን በመሰረዛቸው እንዲሁም የሟች ቤተሰቦች በበኩላቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ካሳ በመጠየቃቸው ነበር።
በአምስት ወራት ልዩነት ከተሰቱት ከላየን እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋዎቹ በኋላ በተደረገ ምርመራ አውሮፕላኖቹ መቆጣጠርያ መስተጋብራቸው ችግር እንዳለበት እንደተደረሰበት ይታወሳል።


















