ለኢትዮጵያና ለኢንዶኔዢያ የአውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች በቦይንግ የቀረበው ካሳ ቁጣን ቀሰቀሰ

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ለተከሰከሱት ሁለት የ737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተጎጂ ቤተሰቦች የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ካሳ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ይህ ገንዘብ በሁለቱ አውሮፕላኖች አደጋ ለሞቱ በድምሩ ለ346 ተጎጂ ቤተሰቦች የሚከፋፈል ሲሆን ገንዘቡ የሟች ቤተሰቦችን የትምህርትና የኑሮ ወጪን የሚሸፍነው ነው ብሏል ቦይንግ።

ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሲከሰከስ የአቶ እያሱ ተሾመ ባለቤት ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዷ ነበሩ። በአደጋውም ህይወታቸው አልፏል።

ከቦይንግ ውሳኔ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡት አቶ እያሱ ''ለእኔ 100 ሚሊየን አይደለም 100 ቢሊየን እንኳን ሚስቴን አይመልስልኝም'' ብለዋል።

''አንድ ድርጀት ችግር ያለበት ምርት ወደገበያ አስገብቶ ቤተሰቦቻችንን ነው ያሳጣን። ይሄ በገንዘብ የሚተካ ወይም የሚተመን አይደለም።''

አቶ እያሱ ጨምረውም "አውሮፕላኑ ችግር እንዳለበት ይታወቃል፤ ከመጀመሪያው አደጋ በኋላ ማስቆም ይችሉ ነበር። እነሱ ግን ትርፋቸውን በማሰብ በሰው ልጅ ህይወት ፈርደዋል።"

የሰው ህይወት በገንዘብ አይለወጥም የሚሉት አቶ እያሱ፤ ገንዘቡን ሳይሆን ከሁሉ በፊት ፍትህን አንደሚፈልጉ በምሬት ይናገራሉ።

ኖሚ ሁሴን በአሜሪካ ቴክሳስ የሚገኙ የህግ ባለሙያ ሲሆኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ያጡ አንዳንድ ቤተሰቦችን በመወከል ጥብቅና ቆመዋል። እሳቸው እንደሚሉት ቦይንግ ያቀረበው ሃሳብ የተጎጂ ቤተሰቦች ያጡትን ነገር ከግምት ውስጥ ያለስገባና ካሳ ለመባል እራሱ ቅርብ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

ጠበቃው ለቢበሲ እንደገለጹት አንዳንዶቹ ደንበኞቻቸው በገንዘብ ካሳው ብዙም ደስተኛ አይደሉም ''ቦይንግ በጥሩ ሁኔታ ሲሸጥ የነበረውን አውሮፕላኑን ለመከላከል በማሰብ በሰው ህይወት ቁማር ተጫውቷል፤ እነሱ ያስቀደሙት ትርፋቸውን ነው'' ብለዋል።

ጠበቃ ሁሴን በሰጡት መረጃ መሰረት እስካሁን ሰባት የተጎጂ ቤተሰቦችን ወክለው ፍርድ ቤት እየተከራከሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደንበኞቻቸው እስከ 276 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ካሳ ጠይቀዋል።

ሌላኛው በአደጋው ባለቤታቸውንና ሦስት ልጆቻቸው ያጡት ኬንያዊው ጆን ኩዊንዶስ በበኩላቸው የተጎጂ ቤተሰቦችን የዋትስአፕ ቡድን ፈጥረው እንደሚገናኙና ምንም አይነት የካሳ ገንዘብ ላለመቀበል መስማማታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቦይንግ እስካሁን በግላቸው እንዳላነጋገራቸውና ስለካሳው በዜና መስማታቸውንም አክለዋል።

የቦይንግ ሊቀ መንበርና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሙይልንበርግ "ቦይንግ በሁለቱም አደጋዎች ለተቀጠፈው የሰዎች ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ አዝኗል። የጠፋው ሕይወት በሚቀጥሉት ዓመታትም የሚረሳ አይሆንም" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ገንዘብ የሟች ቤተሰቦች በፍርድ ቤት ላቀረቡት ክስ የተሰጠ ሳይሆን ድርጅቱ ከፍርድ ሂደቱ ውጭ ያደረገው ክፍያ ነው።