የኢቲ 302 የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፡ አብራሪዎቹ ትክክለኛው ቅድመ ተከተል ተከትለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 አውሮፕላን አደጋ ከደረሰበት ከሃያ አምስት ቀናት በኋላ የምርመራው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ሆኗል።
መጋቢት 1/2011 ዓ.ም ለበረራ መሬትን ከለቀቀ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከሳምንታት በኋላም የዓለም መነጋገሪያ እንደሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የአደጋው ምርመራ ሪፖርት እስከታወቀበት እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ ዘልቋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለዓለም ይፋ የተደረገው ምርመራ ውጤት አውሮፕላኑ እንዲበር የሚያስችለው ፈቃድ እንደነበረው፣ አብራሪዎቹም በቂ ልምድ እና ፍቃድ እንደነበራቸው፣ አውሮፕላኑ ያለችግር በረራውን እንደጀመረ፣ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል ማዘቅዘቁንና ችግር ባጋጠማቸው ወቅትም አብራሪዎቹም የሚጠበቅባቸውን እንዳደረጉ ይሁን እንጂ አውሮፕላኑን መቆጣጠር እንዳልቻሉ አመልክቷል።
ከዚህም በመነሳት የምርመራው ቡድን በአውሮፕላኑ ላይ ያጋጠመው "የፊተኛው ጫፍ ወይም አፍንጫ የመደፈቅ ችግርን" ለመቆጣጠር የሚያስችል የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን አምራቹ እንዲፈትሽ እና ይህንን ችግር ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሥርዓትም በአግባቡ መዘርጋቱን ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ዘመኑ ካፈራቸው እጅግ የረቀቁ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ታላላቅ አየር መንገዶች እንዲኖራቸው የሚፈልጉት የአውሮፕላን አይነት ነው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ያለው እና በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ አየር መንገድም አውሮፕላኑ ካላቸው የአየር ትራንስፖርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው። በተጨማሪም ተገንብተው በተለያዩ ጊዜያት እንዲቀርቡለት ያዘዛቸው ተጨማሪ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች እንዳሉትም ተነግሯል።

የአሜሪካው ግዙፍ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ የተለያዩ አይነት አውሮፕላኖችን የሚያመርት ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ምርቶቹን እያዘመነ ለዘመናት በዓለም የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ተጽእኖ እንደጠበቀ ለመቆየት እየሰራ የሚገኝ ነው። ይህ 737 ማክስ 8 የተሰኘው ስሪትም የዚህ ውጤት ነው።
የአውሮፕላኑ ዘመናዊነት እና ነዳጅ ቆጣቢነት ከባድ ፉክክር ባለበት የአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ አየር መንገዶች ወጪያቸውን ቀንሰው ብቁና ተወዳዳሪ በመሆን ለመዝለቅ እንዲህ አይነቱን አማራጭ መጠቀማቸው የግድ ነው። በዚህም የአውሮፕላኑ ባለቤት ለመሆን የተለያዩ አየር መንገዶች እየተጠባበቁ ባለበት ወቅት ነው ይህ አደጋ ያጋጠመው።
ከወራት በፊት የኢንዶኔዢያው ላየን አየር መንገድ ተመሳሳይ አውሮፕላን በተመሳሳይ ሁኔታ መከስከሱ በአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። አምራቹም ይህንን ለመከላከል የሚያስችል የደህንነት ቅደም ተከተል አስተዋውቆ ነበር።
ነገር ግን በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው ተመሳሳይ አደጋ በአውሮፕላኑ የደህንነት መቆጣጠሪያ ላይ ከባድ ጥያቄን በማስነሳቱ ጉዳዩ በዓለም ዙሪያ ዋነኛ ርዕስ ሆኖ ሁሉም ጥያቄዎች በቦይንግ ኩባንያ ላይ አነጣጥረዋል። ስለአደጋው በምርመራ እስኪታወቅና ደህንነታቸው አስተማማኝ መሆኑ እስኪረጋገጥ አውሮፕላኖቹ ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
ይህም በቦይንግ ላይ ከፍ ያለ ጫናን አስከትሏል። ተመሳሳይ አውሮፕላን እንዲቀርብላቸው ትዕዛዝ ሰጥተው የነበሩ አየር መንገዶችም ጥያቄያቸውን ሰርዘዋል። አደጋው ኩባንያው በዘርፉ ያለውን የደህንነት ብቃት ከጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉ ባሻገር በአክሲዮን ገበያው ያለው ዋጋም እንዲያሽቆለቁል ማድረጉም ተነግሯል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል አደጋውን ተከትሎ በተጓዦች ቁጥር ላይ የታየ ለውጥ እንደሌለ "በአደጋው ቀን ብቻ ሦስት መቶ በረራዎችን" ማስተናገዳቸውን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ወልደማሪያም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አደጋውን ተከትሎ ከአብራሪዎቹ አንጻር የወጡ የተወሰኑ ዘገባዎች ቢኖሩም በርካታዎቹ መረጃዎች ትኩረታቸውን ያደረጉት በአውሮፕላኑ የደህንነት መጠበቂያ ሥርዓት ላይ ነበር። ምንም እንኳን ቦይንግ 737 ማክስ 8 እጅግ ዘመናዊ እንደሆነ ቢነገርም ለእዚህና ቀደም ሲል ላጋጠመው አደጋ ምክንያቱ ተመሳሳይ ነው መባሉ ከፍ ያለ ትኩረትን ስቧል።
ከአደጋው መድረስ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ዛሬ ይፋ የተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤት እንዳመለከተው 157 ሰዎች ለሞቱበት አደጋ ከአብራሪዎቹ በኩል ምንም አይነት ችግር አያመለክትም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በመጀመሪያ ደረጃው ሪፖርት ላይ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች በቦይንግ የሚታዘዘውንና በአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣን ተቀባይነት ያለውን የደህንነት ቅደም ተከተል ተግባራዊ በማድረግ በበረራው ላይ ያጋጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቆጣጠር መጣራቸውን ግልጽ ማድረጉ አስደስቶታል።













