የታንዛንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም አሉ

የታንዛንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የታንዛንያ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም አሉ።

"ትላንት የተካሄደው ምርጫ አልነበረም" ሲሉ በዳሬ ሰላም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ ቅሬታው መሠረት ቢስ ነው ብሏል።

ቱንዱ ሊሱ ከፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊ ጋር ተቀናቃኝ ከነበሩ 14 እጩዎች አንዱ ናቸው።

ማጉፉሊን አንዳንዶች ሲያደንቋቸው፤ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ደግሞ ዴሞክራሲና ነጻነትን አፍነዋል ሲሉ ይተቿቸዋል።

ሌላው ቀንደኛ ተፎካካሪ ማሊም ሰይፍ ሸሪፍ ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከጠሩ በኋላ ታስረዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ሰሚስቶክለስ ካጅጌ ሐሰተኛ ድምጽ መስጫ ተሰራጭቷል የተባለው ውሸት ነው ብለዋል።

ትላንት እና ዛሬም ዋትስአፕ እና ትዊተር መታገዳቸውን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።

የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ ቢሆንም፤ ዛሬ ዛንዚባር ውስጥ አለመረጋጋት እንደነበር ተዘግቧል።

ተቃዋሚው ቱንዱ ሊሱ፤ "በታንዛንያ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረትም የተካሄደው ምርጫ አልነበረም። ሥልጣናቸውን ለመበዝበዝ የወሰኑ ሰዎች ተግባር ነው" ብለዋል።

ብዙዎቹ የፓርቲያቸው አባሎች ለሰዓታት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረዋል። በነዚህ ጣቢያዎች ምርጫው መጭበርበሩንም አክለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምርጫውን ውጤት እንዳይቀበልና ምርጫውን ያጭበረበሩት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አሳስበዋል።

ከ260 የምርጫ ቀጠናዎች መካከል 17ቱ ውጤት በምርጫ ኮሚሽን ድረ ገጽ ላይ ወጥቷል። ማጉፉሊ እየመሩ እንደሆነም ይጠቁማል።

በአብዛኞቹ ቀጠናዎች ማጉፉሊ ከ80 በመቶ በላይ ድምጽ ሲያገኙ በአንድ ቀጠና ደግሞ 99 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

ቅድመ ውጤቱ የቻድማ ፓርቲ መሪ ፍሪማን ምቦዬ መሸነፋቸውንም ያሳያል። መቀመጫውን የወሰዱት የመሪው ሲሲኤም ፓርቲ እጩ ናቸው።