በፈረንሳይ ሦስት ሰዎች በስለት ተወግተው ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Christian Estrosi
በፈረንሳይ ኒስ ከተማ ሦስት ግለሰቦች በስለት ተወግተው መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የከተማዋ ከንቲባ ክርስችን ኤስቶርሲ "ሁሉም ነገር የሚጠቁመው የሽብር ጥቃት እንደሆነ ነው" ብለዋል።
ፖሊስ እንዳለው፤ በጥቃቱ አንድ ሴት አንገቷ በስለት ተቆርጧል። ጥቃቱን አድርሷል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉም ተዘግቧል።
በፈረንሳይ ጸረ ሽብር ላይ አተኩሮ የሚሠራው የዓቃቤ ሕግ ክፍል በግድያ ወንጀል እንደሚጠይቀው ተገልጿል።
ከንቲባው እንዳሉት "ጥቃት አድራሹ በተደጋጋሚ 'አላሁ አክበር' ይል ነበር"።
በጥቃቱ ከተገደሉት አንዱ ባሲሊያ ውስጥ ይሠራ ነበር ተብሏል። ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት አማኞች ሕንፃ ውስጥ እንደነበሩና አንድ የዐይን እማኝ ለአደጋ ጊዜ በተገጠመ መሣሪያ ጥቆማ መስጠቱ ተነግሯል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ጄራልድ ደርሜን ፓሪስ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸው ዜጎች ጥቃት ከደረሰበት አካባቢ እንዲርቁ አሳስበዋል።
ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አካባቢውን እንደሚጎበኙ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዣን ካስቴክስ ኮቪድ-19ን ለመግታት ስለሚታወጀው የእንቅስቃሴ ገደብ መግለጫ ሲሰጡ፤ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል።
"ጉዳዩ አገራችንን የገጠማት አዲስ ፈተና መሆኑ ጥያቄ የለውም" ብለዋል።
የፈረንሳይ የእስልምና ካውንስል ጥቃቱን አውግዞ፤ በጥቃቱ ከተጎዱ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ጎን እንደሚቆም አስታውቋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተማዋ ውስጥ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተሰነዘሩ ነው።
ከአራት ዓመታት በፊት የ31 ዓመት ቱኒዝያዊ በዓል ለማክበር የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በጭነት መኪና ጥቃት አድርሶ 86 ሰዎች ሞተዋል።
ከቀናት በኋላ ጃክዊስ ሀሜል የተባሉ ቄስ ጸሎት እየመሩ ሳለ አንገታቸውን ተቀልተዋል።
በዚህ ወር መባቻ ላይ በሰሜን ምዕራብ ፓሪስ ሳሙኤል ፓቲ የተባለ የታሪክ መምህር መገደሉ ይታወሳል። መምህሩ ከመገደሉ ከቀናት በፊት የነብዩ መሐመድን የካርቱን ሥዕል ለተማሪዎቹ አሳይቶ ነበር።
ጥቃቱ ፈረንሳይ ውስጥ ውጥረት ከማስከተሉ ጎን ለጎን፤ የአገሪቱ መንግሥት አክራሪነትን ለመግታት የሚያደርገው ጥረት ከቱርክ እና ከሌሎች አገሮች መንግሥታት ጋር አጋጭቶታል።
የቱርኩ ፕሬዘዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን የፈረንሳይ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።
የፕሬዘዳንቱ ምስል በፈረንሳዩ የስላቅ መጽሔት ቻርሊ ሄብዶ ላይ መታተሙን ተከትሎ ነገሮች ተካረዋል።












