ኮሮናቫይረስ፡ ማክሮን በፈረንሳይ ሁለተኛ ዙር ብሔራዊ የእንቀስቃሴ ገደብ አወጁ

ጭምብል ያጠለቀች ፈረንሳያዊ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቢያንስ እስከ ህዳር መጨረሻ የሚዘልቅ ብሔራዊ ገደብ ለሁለተኛ ጊዜ ማወጃቸውን አስታውቀዋል ፡፡

በአዲሶቹ እርምጃዎች መሠረት ከአርብ ጀምሮ ሰዎች ለአስፈላጊ ሥራ ወይም ለህክምና ብቻ ከቤት እንዲወጡ ይፈቀዳል ፡፡

በገደቡ መሠረት እንደምግብ ቤቶች እና ቡና ቤቶች ያሉ እና ወሳኝ ያልሆኑ ንግዶች ሲዘጉ ትምህርት ቤቶች እና ፋብሪካዎች ክፍት ሆነው ይቆያሉ።

በቫይረሱ ምክንያት በፈረንሣይ በየቀኑ የሚከሰተው ሞት ከሚያዝያ ወዲህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ማክሰኞ 33 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ፡፡

አገሪቱ "ከመጀመሪያው የሚበልጥ አደጋ እንደተደቀነባት" ማክሮን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀርመን መለስተኛ የተባለ እና ምግብ ቤቶች፣ ጂሞች እና ቲያትሮች መዝጋትን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ገደብ ወስዳለች ፡፡

ቫይረሱ በመላው አውሮፓ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን እንግሊዝን ረቡዕ ዕለት 310 አዲስ ሞት እና 24,701 በቫይረሱ የተያዙ አዲስ ሰዎችን መዝግባለች።

46 ሚሊዮን ፈረንሳዊያንን ጨምሮ የሌሊት እንቅስቃሴዎች በብዙ ሃገራት ታግዷል።

በአውሮፓ ታላላቅ ኢኮኖሚ ባለቤቶች የተገበሩት አዳዲስ ገደቦች የፋይናንስ ገበያው ላይም ከፍተኛ ውድቀት አስከትሏል ፡፡

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን "በሁለተኛው ዙር ውስጥ ነን፡፡ የዘንድሮው የገና በዓል የተለየ ይሆናል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል፡፡

ማክሮን በቴሌቪዥን ብቅ ብለው "በወረርሽኙ መፋጠን ምክንያት እንዳንዋጥ ጨከን ብለን ገደቦችን ተግባራዊ ማድረግ አለብን" ብለዋል ፡፡

"ከታሰበው በከፋ መልኩ ቫይረሱ ባልገመትነው ፍጥነት እየተሰራጨ ነው" ብለዋል ማክሮን።

እንደመጀመሪያው እገዳ ሁሉ በአዲሱ ህጎች መሠረት ሰዎች ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣት ቅጽ መሙላት ይኖርባቸዋል ፡፡ ማህበራዊ ስብሰባዎችም ታግደዋል ፡፡

የህዝብ አገልግሎት ሰጪዎች እና ፋብሪካዎች ክፍት ሆነው እንደሚቀጥሉ በመግለጽ ኢኮኖሚው "መቆምም ሆነ መፍረስ የለበትም" ብለዋል ፡፡

የጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል አገራቸው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመዋጋት እርምጃ መወሰድ አለበት በሚል ጥሪ አቅርበዋል።

ጀርመን ከሌሎች በርካታ የአውሮፓ ክፍሎች አንጻር አነስተኛ ስርጭት መጠን ቢኖራትም ባለፉት ሳምንታት ቫይረሱ የተስፋፋበት ፍጥነት በርሊንን አስጨንቋታል፡

"የጤና ስርዓታችን ለዛሬ ይህንን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም ይችላል። በዚህ የስርጭት ፍጥነት በሳምንታት ውስጥ የአቅም ገደቡ ጫፍ ላይ ይደርሳል" ብለዋል ሜርክል፡፡

የጀርመን መንግሥት ለገና ቤተሰቦች እና ጓደኞች እንዲገናኙ ለማስቻል ከፍተኛ ፍላጎት አለው ቢባልም በየዕለቱ የሚመዘገበው ቁትር ወደ 14 ሺህ 964 ከፍ ሲል በ24 ሰዓታት ውስጥም 85 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል ፡፡