ኮሮናቫይረስ፡ ቻይና በአንድ ሰው ምክንያት የአንድ ከተማ ነዋሪዎችን በጠቅላላ እየመረመረች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና በዢንዣንግ ግዛት በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱን ተከትሎ ለግዛቲቱ ነዋሪዎች በአጠቃላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እያደረገች ነው።
እስካሁን ድረስ 4.7 ሚሊዮን የሚጠጋ የካሽጋር ነዋሪዎች የተመረመሩ ሲሆን፤ 138 ምልክቱን የማያሳዩ ነገር ግን ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ተገኝተዋል ተብሏል።
ቻይና የቫይረሱን ስርጭት በመቆጣጣር ረገድ ውጤታማ ብትሆንም ነገር ግን አልፎ አልፎ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እየተገኙ ነው።
ዢንዣንግ በርካታ ሙስሊም ቻይናውያን የሚገኙ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ቤይዢንግ የመብት ጥሰት ትፈጽምባቸዋለች ሲሉ ይከስሳሉ።
በካሽጋር ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ነዋሪዎቿም ቢሆኑ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ምስክር ወረቀት ካልያዙ በስተቀር ወዴትም መሄድ እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።
በካሽጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ እንዳለባት የተረጋገጠችው ሴት ምንም ዓይነት ምልክት የማታሳይ የነበረች ሲሆን፤ በከተማዋ ዳርቻ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ውስጥ ሰራተኛ ናት ተብሏል።
የቻይና መገናኛ ብዙኀን "ተከታታይነት ያለው ምርመራ" ሲሉ በጠሩት የኮቪድ-19 ምርመራ መሰረት የተመረመረችው ይህች ሴት በቻይና ከ10 ቀን በኋላ የተገኘች የመጀመሪያዋ በቫይረሱ የተያዘች ሴት ሆናለች።
ቅዳሜ እለት የተጀመረው አጠቃላይ ምርመራ እስካሁን ድረስ 138 ምልክቱን የማያሳዩ ነገር ግን ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎችን አግኝቷል።
በቻይና እስከ አሁን ድረስ 85,810 በቫይረሱ መያዛቸው ቢመዘገብም ምልክቱን የማያሳዩ ሰዎች ግን በዚህ ቁጥር ውስት አይካተቱም። እስካሁን ድረስ ቻይና የ4,634 ሰዎችን ህይወት በቫይረሱ ምክንያት አጥታለች።
የከተማዋ ባለስልጣናት እሁድ ከሰዓት በካሽጋር ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮሮናቨይረስ ምርመራ እንደተደረገላቸው ገልፀው፣ ቀሪዎቹ ነዋሪዎች ደግሞ በሁለት ቀናት ውስጥ ተመርምረው ይጠናቀቃል ብለዋል።
በቻይና ሰዎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው የተመለሱ ቢሆንም አሁንም ግን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው እየተገኙ ነው።
ቻይና በፍጥነት ሰፊ እና አጠቃላይ ምርመራ በማካሄድ ቫይረሱን ለመቆጣጣር እየሞከረች ትገኛለች።
ከዚህ ቀደም ብሎ ቂንግዳኦ ከተማ 9 ሚሊዮን ነዋሪዎቿን በአጠቃላይ መርምራለች።
በግንቦት ወር ደግሞ ለመጀመሪያ ገዜ የኮሮናቫይረስ የተገኘባት ዉሃን ከተማ 11 ሚሊዮን ነዋሪዎቿን መርምራለች።
















