ጆን ማጉፉሊ፡ ኮሮናቫይረስን ከአገር አባረዋለሁ ያሉት መሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የኮሮረናቫይረስን በተመለከተ በሚሰጧቸው አስተያየቶችና በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻሉ መሪ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው ለመመረጥ እየሰሩ ነው።
ኮቪድ-19 ታንዛኒያ ሲደርስ ፕሬዚዳንቱ ሰዎች በቤታቸው መቆየት የለባቸውም ብለው አጥብቀው ይከራከሩ ነበር። እንዳውም ቫይረሱ እንዲጠፋ ቤተክርስቲያን እና መስጂድ ሄደው እንዲጸልዩ አበረታትተዋል።
''ኮሮናቫይረስ እርኩስ መንፈስ ነው፤ በክርስቶስ ሰውነት ውስጥ ሊቆይ አይችልም. . . . . ወዲያውኑ ይቃጠላል'' ሲሉም ተደምጠዋል አጥባቂ ክርስቲያኑ መሪ ጆን ማጉፉሊ።
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በተጨማሪ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ስለማድረግ በተመለከተ ሲናገሩ ምንም አይጠቅመንም ብለዋል።
አክለውም የምርመራው እውነተኛነት ላይ ጥርጣሬ እንዳለቸው በመግለጽ በተለያዩ ፍራፍሬዎችና አንዲት ፍየል ላይ ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ በፓፓዬና በፍየሏ ላይ መገኘቱን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ጎረቤት አገራት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸውን በመተቸትም እሳቸው ግን በዚህ መልኩ ኢኮኖሚውን መጉዳት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ በርካታ አወዛጋቢና አነጋጋሪ ውሳኔዎችንም በማሳለፍ ይታወቃሉ። በአገሪቱ ታሪክ ከ54 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የነጻነት ቀን ብዙ ገንዘብ እያስወጣን ስለሆነ በህዝባዊ በአል አናከብረውም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በአሉን በማክበር ፋንታም ህዝቡ ወጥቶ አካባቢውን እንዲያጸዳ ኣደረጉ ሲሆን እራሳቸውም በመንገድ ላይ በመውጣት በእጃቸው ቆሻሻ ሲሰበስቡ ውለዋል በነጻነት ቀን ላይ።
ጆን ማጉፉሊ ፕሬዚዳንቱ በሆኑበት የመጀመሪያ ዓመት ላይ የሚወስዷቸው እርምጃዎች በበርካቶች ዘንድ ሙገሳን አስገኝቶላቸው ነበር።
እንዳውም ታንዛንያውያን በትዊተር በኩል ማጉፉሊ ቢሆኑ ምን ያደርጉ ነበር እያሉ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ሲጋሩት ከርመዋል።
ጉዳዩን ወደ ቀልድ የወሰዱት በርካቶች ቢሆንም ለጊዜውም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ የአገሬውን ዜጋ መነጋገሪያ ጉዳይ ሰጥተውት ነበር። ከአገራቸው አልፎም በጎረቤት አገራት ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር ችለው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2017 አንድ ኬንያዊ ፕሮፌሰር በዳሬሰላም ዩኒቨርሲቲ ንግግር ሲያደርጉ አፍሪካ በማጉፉሊ አስተሳሰብ መቃኘት አለባት ሲሉ ተደምጠው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ነገር ግን ቀስ በቀስ ፕሬዚዳንቱ የነበራቸው ድጋፍና ተቀባይነት እየተሸረሸረ መጥቷል።
የማጉፉሊ አስተዳደር ያልተለመዱና በድፍረት የሚወሰዱ በርካታ ሕጎችንና መመሪያዎችንም ሲያወጣ ነበር። በተለይ ደግሞ ከዓለምአቀፍ የማዕድን አውጭ ተቋማት ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ ያለሙ ሕጎች ተጠቃሽ ናቸው።
2017 ላይ 'አኬሺያ ማይኒንግ' የተባለው ዓለምአቀፍ የማዕድን አውጭ ድርጅት 190 ቢሊየን ዶላር ግብር እንዲከፍል ተጠይቆ የነበረ ሲሆን ከብዙ ክርክር በኋላ ግን ድርጅቱ 300 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል።
በመቀጠልም የታንዛንያ መንግሥት በድርጅቱ 16 በመቶ ድርሻ እንዲኖረውና ወደፊት ለሚገኙ ትርፍና መሰል ጥቅማትቅሞች እኩል ለመካፈል ተስማምተዋል።
ፕሬዚዳንቱን በእጅጉ ከሚያስተቿቸው ውሳኔዎች መካከል ደግሞ ሴት ተማሪዎች በትምሀርት ላይ እያሉ ካረገዙ ተመልሰው ወደ ትምህርት ቤት መግባት አይችሉም የሚለው ነበር።
ኢኮኖሚውን ከማነቃቃት አንጻር ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በርካታ ስራዎችን መስራት ችለዋል። ታንዛንያን ከጎረቤት አገራት የሚገናኘው የባቡር መስመርን ጨምሮ በአገሪቱ አሉ የሚባሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ አድርገዋል።
በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ብሄራዊ አየር መንገድም ከእዳው ተላቆ በአዲስ መልክ እንዲዋቀርና ወደ ገበያ እንዲገባም የሰሩ ሲሆን በአገሪቱ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እስከ አራተኛ ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ትምህርት በነጻ እንዲሰጥ አድርገዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ኮሮረናቫይረስን በመቆጣጠር ረገድ ለወራት ይወስዷቸው የነበሩ እርምጃዎች ከአገሬው ዜጋም ሆነ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ትችትን አስከትሎባቸዋል።
ምንም እንኳን አገሪቱ የመጀመሪያውን የኮሮረናቫይረስ ምልክት ካየች በኋላ ትምህርት ቤቶችን በመዝጋትና ገደቦችን ማስቀመጥ ብትጀምርም የዓለም ጤና ድርጅት ግን ታንዛንያ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የወሰደችው እርምጃ የዘገየና ውጤታማ ያልነበረ ነው ብሏል።
በወቅቱ ገበያዎችና የስራ አካባቢዎች ክፍት የነበሩ ሲሆን የእምነት ቤቶችም ቢሆኑ ለአማኞች ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።
''በአገራችን በርካታ በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎች አሉ፤ እንደ ኤችአይቪ ኤድስ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል። ሁሌም ቢሆን ኢኮኖሚያችን መቅደም አለበት። ኢኮኖሚው እንዲተኛ መፍቀድ የለብንም፤ ሕይወትም መቀጠል አለባት'' ብለው ነበር ፕሬዚዳንቱ።
በተጨማሪም ''ሌሎች የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ቸኩለው በመዝጋታቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለሚገቡ በቅርብ ዓመታት ምግብ ከእኛ ለመግዛት መምጣታቸው አይቀርም'' ሲሉም ተደምጠው ነበር።
በአሁኑ ሰአት ታንዛንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ስትሆን ፕሬዝዳንቱም በድጋሚ ለመመረጥ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ነው።
ዋነኛ ተቀናቃኞቻቸው ደግሞ የቻዴማ ፓርቲ ተወካዩ ቱንዱ ሊሱ ናቸው። ሰውዬው በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው የነበረ ሲሆን ላለፉት ሶስት ዓመታት በውጪ አገር በሕክምናና ማገገም ላይ አተኩረው ቆይተዋል።
በአገሪቱ ታሪክ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የሚመሩት ፓርቲ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሸንፎ አለማወቁ እሳቸውም በድጋሚ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ በርካቶች ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው።
ተቀናቃኛቸው ቱንዱ ሊሱ ደግሞ በአገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሚያደርጉና ሰብአዊ መብት እንዲከበር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ሌላኛው ተፎካካሪ በርናርድ ሜምቤ ደግሞ የቀድሞ ሚኒስትር ሲሆኑ እሳቸውም በምርጫው ካሸነፉ በርካታ ለውጦችን እንደሚያደርጉ እየገለጹ ነው።
ጆን ማጉፉሊ በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ በአገሪቱ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እንደሚያተኩሩና የዜጎችን ኑሮ ለመቀየር በርካታ ፖሊሲዎች ማርቀቅና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።












