ኮሮናቫይረስ፡ በኦክስፎርዱ የክትባት ሙከራ ላይ አንድ ሰው ቢሞትም የደህንነት ስጋት የለበትም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአስትራዜኔካ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በጥምረት እየበለጸገ የሚገኘው የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ ሙከራ በሚደረግባት ብራዚል የአንድ በጎ ፈቃደኛ ሕይወቱ ማለፏን ተከትሎ ክትባቱ ምንም አይነት የድህንነት ስጋት እንደሌለበት ተገለጸ።
የብራዚል ጤና ባለስልጣን ከሙከራው ጋር በተያያዘ ሕይወቱ ስላለፈው በጎ ፈቃደኛ ምንም አይነት መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ እንደሚደረግና ክትባቱ ግን ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንደሌለበት አስታውቋል።
ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሰረት ደግሞ በጎ ፈቃደኘው ክትባቱን አልወሰደም።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየተሰራ የሚገኘው ክትባት ላይ ከሚሳተፉት በጎ ፈቃደኞች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ብቻ ሲሆን ክትባቱን እንዲወስዱ የተደረገው ቀሪዎቹ ደግሞ ማረጋገጫ የተሰጠው የማጅራት ገትር ክትባት ነው የተሰጣቸው።
የሙከራው ተሳታፊ በጎ ፈቃደኞችም እራሳቸው የሚሰጣቸው የኮሮረናቫይረስ ክትባት ይሁን የማጅራት ገትር የሚያውቁት ነገር የለም። ይህ የሚደረገውም በገዛ ፈቃዳቸው ነው ተብሏል።
ግዙፉ የመድሀኒት አምራች አስትራዜኔካ በበኩሉ በእያንዳንዱ የግለሰብ የሙከራ ሂደት ላይ አስተያየት እንደማይሰጥና ሙከራው ሲካሄድ ግን አስፈላጊው ጥንቃቄና የደህንነት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውቋል።
''ሁሉም ወሳኝ የጤና ሁኔታዎች በጥንቃቄ ተመርምረዋል፤ ከግምት ውስጥም ገብተዋል። ሙከራውም ሆነ የምርምር ሂደቱ ምንም አይነት አሳሳቢ ነገር አልተገኘባቸውም፤ የሚመለከታቸው ኃላፊዎችም ሂደቱን እንዲከታተሉት አድርገናል'' ብሏል።
በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው የክትባት ሙከራዎች መካከል ይሄኛው በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በቅርቡ ለገበያ እንደሚበቃም ይጠበቃል።
እስካሁን ደረጃ አንድና ደረጃ ሁለት የሙከራ ሂደቶችን በስኬታማነት ያጠናቀቀው ይኸው ክትባት ደረጃ ሶስትን ለማጠናቀቅ ደግሞ በዩኬ፣ ብራዚልና ሕንድ በበጎ ፈቃደኞች ላይ ሙከራውን እያካሄደ ይገኛል።
ባሳለፍነው ወር በዩኬ ይካሄድ የነበረው ሙከራ የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው ይችላል በሚል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ከቀናት በኋላ ግን ሙከራውን ለማከናወን ምንም ስጋት እንደሌለ በመገለጹ ሂደቱ በድጋሚ እንዲጀመር ሆኗል።
የብራዚል ጤና ባለስልጣን በጎ ፈቃደኛው ሕይወቱ ስለማለፉ ከትናንት በስትያ መስማቱን አስታውቋል።
የብራዚል መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ሕይወቱ ያላፈችው ግለሰብ የ28 ዓመት የህክምና ባለሙያ እንደሆነና ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወቱ እንዳለፈች ዘግበዋል።
ይህ ክትባት ሙሉ ፈቃድ የሚያገኝ ከሆነ ብራዚል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብልቃጦችን ለመግዛት ወስናለች።
በአገሪቱ እስካሁን 5.3 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከአሜሪካና ሕንድ በመቀጠል በዓለማችን ሶስተኛው ከፍተኛ ቁጥር ነው። የሟቾች ቁጥር ደግሞ እስካሁን 155 ሺ መድረሱ ተረጋግጧል።












