ሶማሌ ክልል፡ ኦብነግ የከፍተኛ አመራሮቹ እስር በድርድር ሊፈታ እንደሚችል ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, ONLF
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ሶስት ከፍተኛ አመራሮቹ መታሰራቸውን የፓርቲው ቃለ አቀባይ አብዱልከድር ሀሰን ኢርሞጌ አዳኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉትም የቆራሄ ዞን ሊቀመንበር መሃመድ ጂግሬ ገመዲድ፣ ምክትላቸው ተማም መሃመድ ማህሙድና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉና ለረዥም አመታት በፓርቲው በስራ አስፈፃሚነት የሰሩት መሃመድ ኢብራሂም ሙርሳል ናቸው።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኡመር ፋሩቅ ወርፋም ለቢቢሲ ሶማሊኛ በሰጡት ቃል ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አረጋግጠዋል።
ፓርቲው በትዊተር ገፁም ላይ እንዳሰፈረው በትናንትናው ዕለት፣ ጥቅምት 11/2013 ዓ.ም ልዩ ፖሊስና የቀብሪ ደሃር ፖሊስ መሃመድ ኢብራሂም ሙርሳልን በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
ሌሎቹ አመራሮች ደግሞ ጥቅምት 10/2013 ዓ .ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስፍሮ "ኦብነግ ሰላሙን እያከበረ መሆኑ ክልሉን አበሳጭቷል" ብሏል።
ሶስቱ የፓርቲው ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስመልክቶ "ህገወጥ ነው" በማለትም ቃለ አቀባዩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከሶስት አስርት አመታት በላይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው ግንባሩ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈረመው ከሁለት አመት በፊት ጥቅምት 11፣ 2010 ዓ.ም በአስመራ ነበር።
ይህንንም በማስመልከት በቀብሪዳሃር ከፍተኛ የደስታና የድጋፍ ሰልፍ ከሰሞኑ ተካሂዷል።
ከዚህም በተጨማሪ በቀብሪዳሃር በተከታታይ ኮንፍረንሶችና ስብሰባዎችን ፓርቲው እያካሄደ ሲሆን እነዚህን ስብሰባዎችንም ለማካሄድም ከከተማዋ ምክር ቤት ፈቃድ ማግኘታቸውን ቃለ አቀባዩ ይናገራሉ።
አቶ ኡመር በበኩላቸው ስብሰባው እንደሚደረግ የአካባቢው መስተዳድር እውቅና እንዳልነበረው ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋበት ባለበት ወቅት አስፈላጊው የመከላከል ጥንቃቄ ሳይደረግ በርካታ ሰዎችን በመጥራታቸው ስብሰባው እንዲበተን መደረጉን ገልፀዋል።
ኃላፊው አክለውም ለተሰብሳቢዎቹና አመራሮቹ የሚያደርጉት ውይይት "ሕገወጥ" መሆኑ ሲነገራቸውም ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ እንዳይገቡ በሚከለከሉበት ወቅትም በኃይል ጥሰው ለመግባት መሞከራቸውን ገልፀዋል።
ቃለ አቀባዩ በኃላፊው አባባል አይስማሙም በወቅቱም ህገወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዳልተፈጠሩ እንዲሁም የደረሱ ችግሮችም ሆነ ጉዳቶች አለመኖራቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በፓርቲያቸው፣ በክልሉ መንግሥትና በፌደራል መንግሥት መካከልም ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን ገልፀው በድርድርም እንደሚፈታም ተስፋ እንደሚያደርጉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ኦብነግ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ "የህዝቡን ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት" በክልሉ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በባለፉት ጊዜያትም ውስጥ ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ጋር ተባብረው እየሰሩ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
ሆኖም በባለፉት ሶስት፣ አራት ወራት ግን ከክልሉ መንግሥት በኩል ፓርቲያቸውን ኢላማ ያደረጉ ትንኮሳዎች እንዳሉ ገልፀው በአጠቃላይ በክልሉ ውስጥ ያለው የመንግሥትና ፓርቲያቸው ሰላማዊ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ፍጥጫና ትንኮሳ መኖሩንም አስረድተዋል።
"በሰላማዊ መንገድ እየታገልን ነው ያለነው፤ ክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ጋርም ተባብረን መስረት እንፈልጋለን። ማንኛውም አይነት ትንኮሳም ሆነ ሆነ ጥቃት በምንም መንገድ አስፈላጊ አይደለም። እኛ ሁሌም ቢሆን ለመተባበርና ለመደራደር ዝግጁ ነን ። " ይላሉ
በፓርቲያቸውና በክልሉ መንግሥት ላለው አለመግባባት ዋነኛ ምክንያቶች የሚሏቸወም የክልሉ መንግሥት የመንግሥት ተቋማትን ህገወጥ በሆነ መንገድ በመጠቀም ኢላማ አድርገውናል ይላሉ።
ኦብነግ የአመራሮቹና የአባላቶቹ መታሰር በድርድር ሊፈታ እንደሚችል ገልፆ ጉዳዩ በሰላም መቋጨት ካልቻለ ግን ወደ ፌደራል መንግሥቱ ሊወስደው እንደሚችል አሳውቋል።
ፓርቲያቸው ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ ተባብሮ ለመስራት፣ ያሉትን ችግሮች ህጋዊና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ፅኑ ቁርጠኝነት እንዳለውና በዚህ መንገድ እየሰራም እንደሆነ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኢትዮጵያ ያራዘመችው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ መሆኑን የገለፁት አቶ አብዱልከድር በሰላማዊ ሁኔታ መታገል እንደሚፈልጉና መፍታትም እንደሚቻል ገልፀዋል።
ግንባሩ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ሁኔታ በዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሰ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግም ዝግጁነት እንዳለውም አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የታዩ መሻሻሎች በጎ እንደሆነ የሚናገሩት ቃለ አቀባዩ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ውስጥ የተንሳራፋውን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድና በድርድር መፍታት ይቻላል ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምንና የብሄራዊና የብሄሮች ውይይትም አስፈላጊነትን አስምረዋል።
ኦብነግ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትግል ያደርጉ ከነበሩ አማፂ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን የተመሰረተው በጎሮጎሳውያኑ 1984 ነው። ቡድኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሦስት የፖለቲካ ቡድኖች ከሽብር ቡድን ዝርዝር ውስጥ በፓርላማው ውሳኔ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በውጪ የሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።












