ልደቱ አያሌው፡ የቢሾፍቱ ፖሊስ አቶ ልደቱ የታሰሩት ሕገ መንግሥቱን በመናድ በሚለው ክስ መሆኑን ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, The Reporter
የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ አቶ ልደቱ ሕገወጥ መሳሪያ በመያዝ በሚለው ክስ በዋስ መለቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለፍርድ ቤት አቀረበ።
ፖሊስ ዛሬ፣ ሐሙስ፣ ለፍርድ ቤት ባስገባው ደብዳቤ አቶ ልደቱ አያሌው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያሉት ሕገ መንግሥቱን በመናድ በሚለው ክስ መሆኑን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በ9/2/13 የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ትዕዛዝ መታዘዙንና በዚሁ ትዕዛዝ መሰረት በ10/2/13 በመዝገብ ቁጥር 670/2013 መለቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።።
በምስራቅ ሸዋ ዞን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በሚል አዲስ ክስ ስለተመሰረተባቸው መልሰን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 171/2013 አስረናቸዋል ደብዳቤው እንደሚል አክለው ተናግረዋል።
ደብዳቤው ለተከሳሽ ጠበቆችም በግልባጭ እንዲደርስ የተደረገ ሲሆን በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለ26/2/2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ልደቱ ነገ ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በሚለው ክስ ቀጠሮ ስላላቸው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ አቶ ልደቱ አያሌውን በአንድ መዝገብ ፈትቶ፣ በሌላ ማሰሩን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የሰጠው ትናንት ረብዕ ሰጥቶ ነበር።።
በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ የተሰጠላቸው አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ ማለዳ፣ ጥቅምት 11/2013 ዓ.ም ችሎት ላይ ተገኝተው ነበር።
ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው አቶ ልደቱ ማክሰኞ ዕለት በታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ በዚህ አኳኋን እንደታሰሩ እንደተነገራቸው ለችሎት ካስረዱ በኋላ ነው።
አቶ ልደቱ ትናንት ረብዑ፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተገኙት በ9/2/2013 ዓ. ም ችሎት በቀረቡበት ወቅት የተሰጡት ሁለት ትዕዛዞችን ለመከታተል መሆኑን አቶ አዳነ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
በባለፈው ቀጠሮ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ መቅረባቸውን ያስታወሱት አቶ አዳነ፤ አዛዡ አቶ ልደቱን ያልፈቱበትን ምክንያት ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ፍርድ ቤቱን ስላላሳመነው አቶ ልደቱን ለቅቀው ሪፖርት እንዲያደርጉ አለበለዚያ ግን እርምጃ እንደሚወስድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተናግረዋል።
ሌላው ትዕዛዝ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አቶ ልደቱ ለምን ሊለቀቁ እንዳልቻሉ ቀርቦ ማብራሪያ እንዲሰጥ የሚል ነበር።
በዚሁ መሠረት የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ በአቶ ልደቱ አጃቢ በኩል አቶ ልደቱን ለምን እንዳልለቀቋቸው ምላሽ ሰጥቷል።
የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ አቶ ልደቱን 'ሕገ ወጥ መሣሪያ ይዞ በመገኘት' በተከሰሱበት መዝገብ እንደለቀቃቸው ምላሽ በመስጠት፣ ነገር ግን በሌላ ክስ ስለሚጠየቁ በ13/2/2013 ዓ. ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ስላላቸው አለመለቀቃቸውን አስረድቷል።
አቶ ልደቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ለችሎቱ "ትናንት [ማክሰኞ] ከቀኑ 10 ሰዓት ከ20 ላይ አንድ ፖሊስ መጥቶ 'በዚህኛው መዝገብ ፈትተንሃል በሌላኛው መዝገብ ክስ ታስረሃል፤ ይህንን እንድታውቀው ነው' በሚል ነግሮኝ ከመሄዱ ውጪ አልተለቀኩም" ማለታቸውን አቶ አዳነ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም "በቃል ለቅቄያሁ ማለት አይሠራም፤ በፍርድ ቤቱ ጊዜ መቀለድ አይገባም፤ ስለዚህ ነገ የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ አቶ ልደቱን መልቀቁን በጽሁፍ ማረጋገጫ ጽፎ እንዲያመጣ" በሚል ትዕዛዝ አስተላልፏል።
አቶ ልደቱ በበኩላቸው ያላቸውን ቅሬታ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ እስካሁን እየሄደበት ያለው መንገድ ፍፁም ተገቢነት ያለው ነው ያሉት አቶ ልደቱ፤ ሕግን ለመተርጎም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት በጣም ደስ ይላል ማለታቸውን አቶ አዳነ ተናግረዋል።
ለዚህም ምስጋና በማቅረብ "ግን አሁን በፍርድ ቤቱ ላይ እየተሠራ ያለው አማተሮች የሚሠሩት አይነት ቴአትር ነው" በማለት "በዚህ ሁኔታ በፍትሕ ሥርዓቱ እና በእናንተም ጊዜ ላይ እኔም አብሬ መቀለድ አልፈልግም። ስለዚህ ፖሊስ አልለቅም እንዳለኝ በታሪክ ይመዝገብልኝ። እና ወደ ቀጣዩ የክርክር ምዕራፍ ብንሸጋገር ነው የሚሻለው" የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን አቶ አዳነ ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ "አሁን እየተጣሰ ያለው ሕግ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱም ጭምር ነው" በማለት ባለው አቅም ሁሉ ይህንን ለማስከበር ጥረቱን እንደሚቀጥል ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተወካይ በበኩላቸው አቶ ልደቱ ያልተለቀቁበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ምላሽ ሰጥተዋል።
እነርሱም የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደገለፀው፤ "አቶ ልደቱ ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ክስ ስለተመሰረተባቸው ነው ያልተለቀቁት" የሚል መረጃ ከቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ መረጃ እንደደረሳቸው ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቱ ግን "የምንነጋገረው ስለዚህ መዝገብ ነው" በማለት አቶ ልደቱ በ100 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ተብሎ ለምን አልተለቀቁም? በማለት "በፍርድ ቤቱ ጊዜ ነው የምትቀልዱት። ይህ በፍትሕ ሥርዓቱም በሕገ መንግሥቱም ላይ መቀለድ ነው" ብሏል።
ስለዚህም ነገ አቶ ልደቱ መለቀቃቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ 8 ሰዓት ላይ ይዛችሁ ቅረቡ የሚል ትዕዛዝ ተላልፏል።
አቶ አዳነ "ነገ ደብዳቤውን ጽፈው ይመጣሉ? ጽፈውስ ቢመጡ አቶ ልደቱ ይለቀቃል? የሚለው በኛ እምነት ያንን የሚያደርጉ አይመስለንም። ምክንያቱም አቶ ልደቱ በምንም ተአምር ለአንድና ለሁለት ቀን ብቻ ሳይሆን ለአንድ ደቂቃም ነፃነቱን አንዲያገኝ በመንግሥት በኩል ፍላጎት የለም። አቶ ልደቱ ይለቀቃሉ ብለን እኛም ተስፋ አናደርግም።" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።














