ልደቱ አያሌው፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አቶ ልደቱን እንዲፈታ ታዘዘ

አቶ ልደቱ አያሌው

አቶ ልደቱ አያሌውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከእስር እንዲፈታቸው ፍርድ ቤት ማዘዙን ጠበቃቸው አቶ አብዱልጀባር ሁሴን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጠበቃው አክለውም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አላከበረም የተባለው የቢሾፍቱ መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የወንጀል ምርመራ ኃላፊዎች ችሎት ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ብለዋል።

ለወራት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ፤ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት በ100 ሺህ ብር በዋስትና ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኖ ነበረ ቢሆንም የቢሾፍቱ መምሪያ ፖሊስ ግን ሳይለቃቸው ቆይቷል።

በወቅቱም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አቶ ልደቱን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ፤ አላስፈላጊ እስር ማስቀረትና የዋስትና መብት ማክብር ያስፈልጋል ሲል ጠይቋል።

አቶ ልደቱ በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ መስከረም 12/2013 ዓ. ም ትዕዛዝ ቢሰጥም እስካሁን አልተፈቱም።

አቶ ልደቱ ዛሬ ረፋድ ላይ የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ የተሰጡ ሁለት ትዕዛዞችን ለማየት እንደሆነ ጠበቃቸው አቶ አብዱልጀባር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ልደቱ ማለዳ 4፡30 ላይ ችሎት ፊት መቅረባቸውን አስታውሰው፤ ችሎቱም ሁለቱን ጉዳዮች በማየት ትዕዛዝ አስተላልፏል ብለዋል።

አንደኛው ሕገ ወጥ መሳሪያ በመያዝ የቀረበባቸውን ክስ ላይ አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች ለማሰማት የነበረ ሲሆን ሶስት ምስክሮችም ቀርበው መስክረዋል።

ሌላኛው ደግሞ ከዚህ በፊት የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም መምሪያው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አልቀበልም በማለቱ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መጥሪያውን አድርሶ፤ ስለማድረሱ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቅ መቀጠሩን ጠበቃው ይገልጻሉ።

በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የተላከውን መጥሪያ ተቀብሎ ያደረሰ ቢሆንም ነገር ግን ለቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ስለማድረሱ ደብዳቤ አልጻፈም ነበር ብለዋል።

ኃላፊውም ችሎት ፊት ያልቀረቡ ሲሆን አቶ ልደቱንም ወደ ችሎት ይዘው የመጡት ፖሊስ ለመምሪያው አዲስ ኃላፊ መመደቡን እና እርሳቸው ይህንን ጉዳይ እንደማያውቁ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ ይህንን ተከትሎም ሁለት ትዕዛዝ መስጠቱን ጠበቃ አብዱልጀባር ይናገራሉ።

አንደኛው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የወንጀል ምርመራ ኃላፊው መስከረም 13፣ 14 እንዲሁም በ26 እና በ27 ሲሰጡ የነበሩ ትዕዛዞች ፖሊስ ሳይቀበል በመቅረቱ እነዚህን የፍርድ ቤት ትዕዛዞች እስካሁን ለምን እንዳልተፈፀሙ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ አዝዟል።

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፍርድ በቶች ትዕዛዝ ሊከበሩ ይገባል ያለው ችሎቱ፤ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ትዕዛዙን አልቀበልም ካለ የበላይ አካሉ የፖሊስ ኮሚሽኑ ኃላፊነት ሊወስድ ስለሚገባ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሸን በአስቸኳይ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አቶ ልደቱን እንዲፈታ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ዛሬ አቃቤ ሕግ ያሰማቸው ምስክሮች ቃላቸው የሰፈረው በትርጉም በመሆኑ ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ከመዝገብ ጋር እንዲያያዝ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ አስቀድሞ ተጽፎ የሚቀርብ በመመርመር ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የወንጀል ምርመራ ኃላፊውን ደግሞ ጥቅምት 9፣ 2013 ዓ. ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷል።