የአፍሪካ ህብረት በናይጄሪያ ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ

ተቃዋሚ ሰልፈኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም የወጡ ናይጄሪያውያን ላይ የደረሰውን ጥቃት የአፍሪካ ህብረት በፅኑ አውግዞታል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በአገሪቱ ውሰጥ ላሉ የፖለቲካና ማህበራዊ ባለድርሻ አካላት "ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅና ሕግም እንዲከበር" የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን በማሰር፣ በማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚል ከፍተኛ ውግዘት እየቀረበበት ያለውና ዘረፋን ለማስቆም የተመሰረተው ልዩ የፌደራል ፖሊስ ኃይል ወይም ሳርስ እንዲበተን ጠይቀዋል ።

ከዚህም በተጨማሪ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለዋል የሚባሉ የፖሊስ አባላትም ምርመራ እንዲከፈትባቸውና ወደ ፍርድ እንዲቀርቡም አሳሳስበዋል።

ናይጄሪያ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በበኩሉ ተቃዋሚዎችና የናይጄሪያ መንግሥት በውይይት ሊፈቱት ይገባል ብሏል።

ኢኮዋስ ተቃውሞው በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ሁለቱም አካላት ኃይል መጠቀም እንደማይገባቸው አሳውቋል።

"ተቃዋሚዎቹ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሰልፋቸውን እንዲያካሂዱና የናይጄሪያም የፀጥታ ኃይሎች ሰልፈኞቹ ላይ ኃይልን ከመጠቀም እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን" ይላል ኢኮዋስ ያወጣው መግለጫ

በናይጄሪያ የፖሊስን የጭካኔ በትር ተማርረው የወጡ ተቃዋሚዎች ጎዳና ላይ መውጣታቸውን ተከትሎ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎችን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ ኢኮዋስ ዝምታን መርጠዋል ተብለው ተተችተዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ማክሰኞ እለት፣ ጥቅምት 10/ 2013 በንግድ ማዕከሏ ሌጎስ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 12 መድረሱን አሳውቋል።

የናይጄሪያ ጦር በበኩሉ ሪፖርቱ ሃሰተኛ ዜና ነው በማለት አጣጥሎታል።

ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ቢደረግም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተሰማሩና እየተመደቡ ነው የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸውን ተከትሎም እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።

ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸውም እያሉ ነው።

ከሰሞኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።