በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት የማሊ ፕሬዚዳንት ከምዕራብ አፍሪካ ልዑካን ጋር ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, ANNIE RISEMBERG
ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ልዑካን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ማሊን ጎብኝተዋል።
በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድ ላክ ጆናታን የሚመራው የልዑካን ቡድን ስልጣኑን ከተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይልና ከስልጣን ከተወገዱት ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ጋር ተወያይተዋል።
"ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታን አግኝተናቸዋል፤ በጥሩ ሁኔታም ላይ ናቸው" በማለት ፕሬዚዳንት ጉድ ላክ ጆናታን መናገራቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስነብቧል።
ከወታደራዊው ኃይል ጋር የሚደረጉት ድርድሮች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ እንደሆነና ተስፋም እንደሰጣቸው "ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ነግረውኛል" ብለዋል ጉድ ላክ ጆናታን።
ኢኮዋስ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያን አስተላልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ አገራት ድንበሮቻቸውን እንዲዘጉ አድርጓል፤ ማንኛውንም የገንዘብ እንቅስቃሴም የገደበ ሲሆን ከማህበረሰቡም የውሳኔ ሰጭነት ቦታ እንድትገለል ወስኗል።
ሆኖም በመፈንቅለ መንግሥቱ የተደሰቱ ማሊያውያን በመዲናዋ ባማኮ ጎዳናዎች በመውጣት ድጋፋቸውን ለወታደራዊው ኃይል አሳይተዋል።
ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈባቸውን የተቃውሞ ሰልፎች መርተዋል።
በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ህግን በተመለከተ ተቃውሞን ከማሰማት ባለፈ የሁሉም መሰረታዊ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ነበር።
አስተዳደራቸው በርካታ የሙስና ቅሌቶችን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን የመስረተ ልማቶች ችግር ብዙዎችን አስመርሯል። በተለይም አርሶ አደሮች የማዳበሪያ እጥረት ማጋጠሙ ቀውስን አስከትሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ሰራዊት ፅንፈኛ አክራሪዎች ጋር በሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሚከፈላቸው ክፍያ ትንሽ መሆኑ ቁጣን ፈጥሯል።












