ማሊ ከአፍሪካ ህብረት አባልነት ታገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ህብረት የፀጥታና ሰላም ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት በመፈንቅለ መንግሥት ፕሬዚዳንቷን ከስልጣን ያስወገደችውን ማሊን ከአፍሪካ ህብረት አባልነት አግዷታል።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አገሪቷ ህገ መንግሥታዊ ስርአት እስክታሰፍን ድረስና በቁጥጥር ስር ያሉትን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎች ባለስልጣኖች እስኪለቀቁ ድረስም እግዱ ይቆያል ብሏል።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳም በወታደራዊ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ያሉትን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታም እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
ሊቀ መንበሩ ሲሪል ራማፎሳ አገሪቷ በአስቸኳይ ወደ ሲቪል አስተዳዳር እንድትመለስም አሳስበዋል።
የአውሮፓ ህብረትም ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር እንዲለቀቁ መጠየቁን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።
በትናንትናው ዕለት ወታደሮች የፕሬዚዳንቱን ቢሮ ሰብረው በመግባት ፕሬዚዳንቱንና አብረዋቸው የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ከነሱም በተጨማሪ የብሔራዊ ጉባኤ ቃለ አቀባይ የሆነው የፕሬዚዳንቱ ልጅ፣ የውጭ ጉዳይና የገንዘብ ሚኒስትሮችም በቁጥጥር ስር መሆናቸውም ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ከስልጣን መልቀቃቸውንም ትናንት አጠር ባለው የቴሌቪዥን መግለጫቸው አስታውቀዋል።












