ማሊ፡ በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማሊ ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ባውባካር ኬታ ‹‹ሥልጣን ለቅቂያለሁ፣ ፓርላማውንም በትኛለሁ፤ ይህን የማደርገው ደም አይፍሰስ ብዬ ነው›› ብለዋል በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት ባመጹ በገዛ ወታደሮቻቸው ከታገቱ በኋላ ነው፡፡
‹‹እኔ ሥልጣን ላይ ለማቆየት ተብሎ ለምን ደም ይፈሳል?››
ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ባቦ በወታደሮች ታግተው ዋና ከተማዋ ባማኮ አቅራቢያ ወደሚገኝ የወታደር ካምፕ ውስጥ ተወስደዋል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ነበር፡፡
አገሪቱ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያላት ፈረንሳይና የአካባቢው አገራት መፈንቅለ መንግሥቱን አውግዘዋል፡፡
‹‹ዛሬ የተወሰኑ ታጣቂ ወታደሮች ሁኔታዎች እንዲለወጡ ጣልቃ ገብተው ካገቱኝ፣ የቀረኝ አማራጭ አለ ወይ?›› ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ከታገቱበት ሆነው፡፡
በአገሪቱ ወታደሮች ዘንድ ከከፍያ መዘግየት ጋር በተያያዘ እንዲሁም ከጂሀዲስቶች ጋር በሚደረግ የተራዘመ ጦርነት ምክንያት መሰላቸትና ቁጣ እንደነበር ይነገራል፡፡
ማሊ ከፍተኛ የድህነት አዘቅት ውስጥ ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ተርታ ትመደባለች፡፡
ፕሬዝዳንት ኬታ ለ2ኛ ጊዜ ምርጫ አሸነፍኩ ያሉት በ2018 ዓ.ም ነበር፡፡ ሆኖም በጥቅሉ በተፍረከረከው መንግሥታዊ አስተዳደራቸው ላይ እንዲሁም በዛች አገር በተንሰራፋ ንቅዘት እና የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት በማሊ ሕዝብ ዘንድ ቅሬታ አድሮ ቆይቷል፡፡
ለዚያም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተከታታይ ተቃውሞዎች ይደረጉ የነበረው፡፡ በኢማም መሐመድ ዲኮ የሚመራው አዲሱ የተቃዋሚዎች ጥምረት ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መፈንቅለ መንግሥቱን ማን መራው?
የካቲ ወታደራዊ ካምፕ ምክትል ኃላፊ ኮሌኔል ማሊክ ዳያው ከጥቂት ኮማንደሮች እና ከጄኔራል ሳዲዮ ካማራ ጋር በመሆን ነው ይህንን ስዒረ መንግሥት ያሳኩት ይላል የቢቢሲ አፍሪቅ ዘጋቢ አብዱል ባ ከባማኮ ባስተላለፈው ዘገባ፡፡
ካቲ ወታደራዊ ካምፕ የሚገኘው ከባማኮ 15 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው፡፡
መጀመርያ ይህንን ካምፕ ከተቆጣጠሩ በኋላ ነበር ወታደሮቹ ወደ ዋና ከተማዋ ዘልቀው ፕሬዝዳንቱን ማገት የቻሉት፡፡
ወታደሮቹ ወደ ከተማው ሲጓዙ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉን ሲሰጣቸው ታይቷል፡፡
ማክሰኞ ከሰዓቱን የፕሬዝዳንቱን ቤት ሰብረው በመግባት ፕሬዝዳንቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በቁጥጥር ሥር አድርገዋል፡፡ በአጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በፕሬዝዳንቱ መኖርያ ቤት ነበሩ፡፡
የብሔራዊ ምክር ቤቱ አፈጉባኤ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልጅ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የፋይናንስ ሚኒስትሩም በወታደሮቹ ታግተዋል፡፡
በዚህ የወታደሮች አመጽ ውስጥ ምን ያህል ወታደሮች ናቸው የተሳተፉት የሚለው ገና ምላሽ አላገኘም፡፡
የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወታደሮቹን ድርጊት አውግዘው የታገቱት ባለሥልጣናት በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
የምዕራብ አፍሪካ ኮሚኒቲ የትብብር መድረክ (ኢኮዋስ) በበኩሉ ሁሉም አባል አገራት ከማሊ ጋር ያላቸውን ድንበር እንዲዘጉ ወስኗል፡፡ ማንኛውም ገንዘብና የንግድ ትስስር ለጊዜው እንዲቆምም አዟል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ለዛሬ ጠርቷል፡፡
ማሊን በቅኝ የገዛቻት ፈረንሳይ መፈንቅለ መንግሥቱን ለማውገዝ የቀደማት የለም፡፡ የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር የማሊ አማጺ ወታደሮች ወደ ካምፓቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡
ፈረንሳይ በሳሀል ክልል ጽንፈኛ ኢስላማዊ ሰርጎ ገቦችን ለማጥፋት በሚል በማሊ ወታደሮቿን አስፍራለች፡፡

















