በማሊ ታጣቂዎች 53 ወታደሮችን ገደሉ

ባለፉት አሥር ዓመታት ከደረሱ ጥቃሮች ይህኛው የከፋ መሆኑ ተገልጿል

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty

በሰሜን ምሥራቅ ማሊ ታጣቂዎች 53 ወታደሮች መግደላቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ። ባለፉት አሥር ዓመታት ከደረሱ ጥቃሮች ይህኛው የከፋ መሆኑም ተገልጿል።

የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል የደረሰው "የሽብር ጥቃት ነው" ሲል በትዊተር በኩል ገልጿል።

እስላማዊ ታጣቂዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2012 ላይ ሰሜናዊ ማሊን ሲቆጣጠሩ ማሊ ሰላሟን አጥታ ነበር። የማሊ ወታደሮች ከፈረንሳይ ወታደሮች ጋር በመተባበር አካባቢውን ከታጣቂዎቹ ቢያስለቅቁም አሁንም የደህንት ጥያቄዎች ይነሳሉ።

ከጥቃቱ አሥር ሰዎች ቢተርፉም፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንደገጠማቸው የማሊ ቃል አቀባይ ያያ ሳንጋሬ ተናግረዋል።

መናካ በተባለው አካባቢ ለደረሰው ጥቃት እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።

መስከረም መጨረሻ ላይ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ባለው የድንበር አካባቢ የሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ በደረሰው ጥቃት 38 ወታደሮች መገደላቸው ይታወሳል።

ፈረንሳይ የምትደግፈው 'ጂ5 ሳሀል' የተባለው የጸረ ሰላም ኃይሎች መካች ቡድን ውስጥ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቻድ፣ ኒጀር እና ሞሪታንያ ይገኙበታል። አምስቱ አገራት መስከረም ላይ ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት 'አናሳሩል ኢስላም' የተባለው ቡድን አባላትን ነው።

ቡድኑ 2016 ላይ የተመሰረተው በጽንፈኛው ሰባኪ ኢብራሂም ማላም ዲኮ ሲሆን፤ ሰባኪው 2012 ላይ በሰሜን ማሊ ከታጣቂዎች ጋር መዋጋቱ ይነገራል።