የማሊ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የአገሪቱን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ወረሩ

ተቃዋሚ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ማሊ ውስጥ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ዋና ከተማዋ ባማኮ የሚገኘውን ብሔራዊውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ተቆጣጠሩ።

ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን ጥይትና አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል። አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ወደ ብሔራዊው ምክር ቤት ጥሰው ለመግባት ሲሞክሩ ታይተዋል።

ሰልፈኞቹ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦባካር ኬይታ ከሥልጣን ይወረዱ ብለው አመፅ ሲጠሩ ይህ በአንድ ወር ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

ተቃዋማዊች፤ የኬይታ መንግሥት እስላማዊ ታጣቂዎችን ማስወገድ አልቻለም፣ የምጣኔ ሃብት ቀውሱን አልፈታም እንዲሁም የምክር ቤት ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ ይወቅሳሉ።

ወግ አጥባቂው ኢማም፤ ማሓሜድ ዲኮ የሚመሩት አዲስ ተቀናቃኝ ፓርቲ በዚህ ሳምንት 'ኬይታ ከሥልጣን ይውረዱ የሚለውን ጥያቄዬን አንስቻለሁ' ሲል ተደምጧል። ቢሆንም በአገሪቱ አሁንም በርካታ ለውጦች ያስፈልጋሉ ይላል ፓርቲው።

የፕሬዝዳንት ኬይታ አስተዳደር ከአዲሱ ፓርቲ ጋር ተጣምሮ የቅንጅት መንግሥት ለመመሥት ያቀረበውን ጥያቄ የኢማሙ ፓርቲ አልቀበልም ብሏል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የባማኮን መንገዶች ዘግተው የፕሬዝደንት ኬይታ መንግሥት ሥልጣን ይልቀቅ የሚለውን ጥያቄያቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ሰልፈኞች መካከል ነው የተወሰኑት ወደ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው [ኦአርቲኤም] በኃይል ዘልቀው የገቡት። በዚህም ጣቢያው ለተወሰነ ጊዜ ሥርጭቱን ለማቋረጥ ተገዶ ነበር።

የተወሰኑ ወጣቶች ንበረት ማውደማቸውም ተዘግቧል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት ለመግባት ከሞከሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች መካከል ቢያንስ አንድ ሰው ተገድሏል።

ማሊ ውስጥ ተቃውሞዎች መሰማት የጀመሩት መጋቢት ወር ላይ ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት ከነበረው የምክር ቤት ምርጫ ውጤት ይዞ ከመጣው መዘዝ በኋላ ነው።

ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን ባይወርዱ እንኳ ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ተቃውሟችሁን አሰሙ ሲል ለደጋፊዎቹ ጥሪ አቅርቧል።

ፕሬዝዳንት ኬይታ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱን ለአምስት ዓመት ለማስተዳደር የተመረጡት። ነገር ግን በአገሪቱ የጂሃዲስት ኃይሎች ጥቃት እየበረከተ መምጣቱ እና የምጣኔ ሃብት ቀውስ መሰከቱን ተከትሎ ተቃውሞዎች እየበረቱባቸው ነው።

በአሁኑ ጊዜ ጂሃዲስት ኃይሎች በማዕከላዊና ሰሜን ማሊ ጥቃት እያደረሱ ነው። ታጣቂዎቹ ይህን ተቃውሞ ተጠቅመው በአገሪቱ ብጥብጥ እንዲስፋፋ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።