በቫይረሱ ምክንያት በቤት እስር የቆየው የቀድሞ የትራምፕ ጠበቃ እስር ቤት ተመለሰ

ማይክል ኮኸን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፕሬዚዳንት ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃ ማይክል ኮኸን ወደ እስር ቤት ተመለሰ።

ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በተያያዘ ህጋዊ ያልሆነ ክፍያ ፈፅሟል በሚል የሶስት አመት እስር ተፈርዶበት ያለው ማይክል ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ስጋት በግንቦት ወር ተለቆ በቤቱ እንዲወሰን ትዕዛዝ ተላልፎለት ነበር።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት ጠበቃው የቤት እስሩን ሁኔታዎች በመጣሱ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል።

የማይክል ኮኸን ጠበቃ ጄፍሪ ሌቪን በበኩሉ ደንበኛው ለተለያዩ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ መስጠትም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መፃፍ ተከልክሎ ነበር ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከሰሞኑም ከባለቤቱና ከባልና ሚስት ጓደኞቹ ጋር ማንሃተን በሚገኝ ሬስቶራንት ውስጥ እራት ሲበላ መታየቱ ጋር ተያይዞም ነው በቤት መወሰኑን መመሪያ ተላልፎ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ የተወሰነው።

ማይክል የነበረበት እስር ቤት በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎም ነበር በቤቱ እንዲቀመጥ የተወሰነው

በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦም ውሳኔው እንዲቀለበስና በቤቱ ውስጥ የመወሰን ሁኔታ እንዲከበርለትም ለማድረግ እንደሞከረም ተዘግቧል።

ከፈደራል እስር ቤቶች ቢሮ የወጣው መግለጫው እንደሚያትተው "በቤት ውስጥ እንዲወሰን ትዕዛዝ ቢተላለፍለትም ይህንን ስለጣሰ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ አድርገናል" ይላል።

የማይክል ጠበቃ በበኩሉ ውጭ ወጥቶ ሬስቶራንት ምግብ የመብላቱን ሁኔታ ምንም መመሪያ የሚጥስ አይደለም ብሎ የተከላከለ ሲሆን ለሚዲያዎች አትናገር ብሎ መከልከሉም የደንበኛውን መብት የሚጥስ ነው ብሏል።

የአምሳ ሶስት አመቱ ማይክል ከሶስት አመታት በፊት በነበረው ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ መግባት አለመግባቷን በሚመረምረው አካል ባደረገው ማጣራት የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ እንዳይበላሽ በሚል ከፕሬዚዳንቱ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ሁለት ሴቶችን ዝም ለማስባል ክፍያ መፈፀሙ ተገልጿል።

እንዲሁም ከፕሬዚዳንቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የግብርና የባንክ ማጭበርበር ተግባራትን ፈፅሟል በሚልም ነው ለእስር የተዳረገው።