በሰሜን አፍሪካ የአል-ቃይዳ መሪ መገደሉን ፈረንሳይ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ማሊ ውስጥ በተካሄደ ዘመቻ በሰሜን አፍሪካ የአል-ቃይዳ መሪ የነበረው አብድልማሊክ ድሮክዴል መገደሉን ፈረንሳይ አስታወቀች።
የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስትር ፍሎረንስ ፓርሊ እንዳሉት ድሮክዴል እና የቅርብ አጋሮቹ በዕለተ ረቡዕ በሰሜናዊ ማሊ በተደረገ ዘመቻ ተገድለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም በሌላ ዘመቻ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን አዛዥ የሆነ ሰው በፈረንጆቹ ወርሃ ግንቦት ላይ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቀዋል።
"በኃያልነት የተወጣናቸው ዘመቻዎች ለአሸባሪ ቡድኖቹ ትልቅ ኪሳራ ናቸው" ሲሉ ሚኒስትሯ የዘመቻውን ውጤት ተናግረዋል።
አክለውም "ጦራችን ከሳህል አጋሮቻችን ጋር በመሆን ቡድኖቹን የማደን ተግባሩን ይገፋበታል" ይላሉ።
በእስልማዊ ማግሬብ የአል-ቃይዳ መሪ የሆነው አብድልማሊክ በሰሜናዊ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አስተባባሪ ነበር። አልፎም የአል-ቃይዳ አጋር የሆነው ጃማት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊም አዛዥም ነበር።
የኢስላሚክ ስቴት ቡድን አለቃ የሆነውና በዘመቻው በቁጥጥር ስር የዋለው ሞሐመድ ምራባት ደግሞ በታላቁ ሰሃራ የኢስላሚክ ስቴት ከፍተኛ ሹም ነበር፤ በቁጥጥር ሥር የዋለው ግንቦት 11 ቀን ነው ይላል ሚኒስትሯ ያወጡት መግለጫ።
ወርሃ ግንቦት መጀመሪያ አካባቢ አይኤስ ታጣቂዎቹ ከአል-ቃይዳ ጋር ማሊና ቡርኪናፋሶ ውስጥ የለየለት ጦርነት ውስጥ እንደገቡ አስታውቆ ነበር። አይኤስ፤ ጃማት ኑስራት ግዛቴን ነቅንቋል፣ የነዳጅ መስመሬን አቋርጧል እንዲሁም ደጋፊዎቼን አስሯል ሲል ይወቅሳል።
አብድልማሊክ ድሮክዴል ማነው?
በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንዳለ የሚነግርለት አብድልማሊክ አፍጋኒስታን ውስጥ የሶቪዬት ወታደሮችን ተዋግቷል። ዓላማው እንደ ቀድሞው በኢራቅ የአል-ቃይዳ መሪ አቡ ሙሳብ አል-ዛርቃዊ መሆን እንደነበርም ይነገራል።
በእስላማዊ ማግሬብ የአል-ቃይዳ መሪ ሆኖ ሳለ ከአራት ዓመታት በፊት በቡርኪናፋሶ ኦጋዱጉ በፈፀመው ጥቃት 30 ሰዎች ሞተው 150 መጎዳታቸው አይዘነጋም።
ከስምንት ዓመታት በፊት አልጄሪያ ውስጥ በሌለበት የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል። የአሸባሪ ቡድን አባል ነው እንዲሁም ፈንጂ በመጠቀም ጥቃቶች ፈፅሟል የሚሉ ክሶች ነበር የቀረረቡበት።
ከዚያ በኋላ አልጄሪያ ውስጥ በእሱ መሪነት በተፈፀሙ ጥቃቶች 22 ሰዎች ሲሞቱ 200 ያክል ሰዎች ቆስለዋል።
አልጄሪያዊ ዜግነት ያለው አብድልማሊክ በሰሜናዊ አፍሪካና ሰሃራ ክልል እጅግ ስሙ የገነነ ነው ይባልለታል። አልጄሪያ ውስጥ ከአንድም ሁለት ሦስቴ ጥቃቶች ፈፅሟል። ማሊ ውስጥ የሰፈሩ የፈረንሳይና የሌሎች አገራት ወታደሮችም ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።
የተባበሩት መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት አብድልማሊክ ፈንጂዎችን በመስራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችን ገድሏል ይላል። ቱኒዚያ፣ ኒጀርና ማሊ ውስጥ የምዕራብ አገራት ዜጎችን በማፈንም ይፈለግ ነበር።
ጂሃዲስት ቡድኖች በባሕሪያቸው መሪ ሲገደል ተተኪውን ወዲያውኑ ያሳውቃሉ። ነገር ግን በሰሜን አፍሪካ በአል-ቃይዳና በኢስላሚክ ስቴት መካከል ከበድ ያለ ውጥረት በመኖሩ የአብድልማሊክ ሞት ዜና እንዲሰማ አልተፈለገም።
የማሊ ቅኝ ገዢ የነበረችው ፈረንሳይ ማሊ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አስፍራለች። ወታደሮቹ ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት በሚል ነው የሰፈሩት።












