ከማሊው መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ ያሉት እነማን ናቸው?

ኮሎኔል ማሊክ ዲያው

የፎቶው ባለመብት, EPA

በትናንትናው ዕለት የማሊ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባቸው ከስልጣን ተወግደዋል። ለመሆኑ ከዚህ መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ እነማን አሉ?

መፈንቅለ መንግሥቱን ካቀነባበሩት መካከል አንድ የወታደራዊ ማሰልጠኛ አካዳሚ ምክትል ኃላፊና በፈረንሳይ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ጄኔራሎች አሉበት ።

በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ቁልፍ ሚናን ከተጫወቱት መካከል የሶስቱን ማንነት እነሆ

  • ኮሎኔል ማሊክ ዲያው

ካቲ የተባለ የጦር አካዳሚ ምክትል አሰልጣኝ ሲሆኑ፤ መፈንቅለ መንግሥቱም እዚህ ቦታ ነው የተጀመረው።

ስለ ኮሎኔሉ ጥልቅ የሚባል መረጃ ባይኖርም በቅርቡ ከሩሲያ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው እንደተመለሱ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ኢስማኤል ዋጌ በዛሬው ዕለት የአገሪቱን ስልጣን ወታደራዊ ኃይሉ እንደተቆጣጠረ መግለጫውን ሲያነቡ ኮሎኔል ማሊክ ከጎናቸው ቆመው ነበር።

"ኮሎኔል ማሊክ ከመዲናዋ ባማኮ 15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የካቲ ወታደራዊ ማሰልጠኛ አካዳሚ ላይ የተነሳው አመፅን መሪ ናቸው። ፕሬዚዳንቱ ከስምንት ሰዓት በፊት ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡም ትእዛዝ ያስተላለፉት እኚሁ ኮሎኔል ናቸው" በማለት ኮሎኔሉ ስለነበራቸው ሚና የወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።

  • ኮሎኔል ሳዲዮ ካማራ

የካቲ ወታደራዊ ማሰልጠኛ አካዳሚ የቀድሞ ዳይሬክተር ነበሩ ኮሎኔል ሳዲዮ

በማሊ ደቡባዊ ክፍል ኩሊኮሮ ግዛት፣ በካቲ በጎርጎሳውያኑ 1979 መወለዳቸውን ማሊ ትሪቡን ድረገፅ አስነብቧል።

ከኮሊኮሮ ወታደራዊ ማሰልጠኛ አካዳሚም በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል። በሰሜናዊ ማሊም ተመድበው በጄኔል ኤል ሃጂ ጋሙ ስር እስከ ጎርጎሳውያኑ 2012 ድረስም አገልግለዋል፥

በኋላም በካቲ ወታደራዊ ማሰልጠኛ አካዳሚ ዳይሬክተር የሆኑ ሲሆን እስከያዝነው አመት ጥር ወር ድረስ፣ ለሩሲያ ወታደራዊ ስልጠና እስከሄዱበት ወቅት በዚሁ ኃላፊነታቸው እያገለገሉ ነበር።

ከሩሲያ የተመለሱት በዚህ ወር ሲሆን ለአንድ ወርም ያህል ፈቃድ ላይ እንደነበሩ ማሊ ትሪቡውን ዘግቧል።

"ኮሎኔል ሳዲዮ በሁሉም ዘንድ የተከበሩ፣ የሚሞገሱና የተወደዱ ናቸው ። በስራቸው ላሉት ወታደሮችም ቀጥተኛነትን፣ ፅናትንና ቁርጠኝነት ተምሳሌት ናቸው" በማለትም ድረ ገፁ ስለባህርያቸው መረጃን አስፍሯል።

  • ጄኔራል ሼክ ፋንታ ማዲ ዴምቤሌ
ጄኔራል ሼክ ፋንታ ማዲ ዴምቤሌ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ጄኔራል ሼክ ፋንታ ማዲ ዴምቤሌ አሊዩኔ ብሎንዲን ቤዬ የተባለ የሰላም አስጠባቂ ተቋም ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው። ከሁለት አመታት በፊት የብርጋዲየር ጄኔራል ማዕረግን ያገኙት ሼክ ፋንታ የተቋሙም መሪ የሆኑት በዚሁ ወቅት ነው።

ጄኔራሉ በዚህ ተቋም ከመሾማቸው በፊት በአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽን ግጭት አፈታት ስልታዊ ዕቅድን የተመለከተውን ቢሮ ይመሩ ነበር ተብሏል። በዚህ ወቅትም መቀመጫቸው አዲስ አበባ ነበር።

ጄኔራል ዴምቤሌ በፈረንሳይ የሚገኝ ሴይት ሲር የጦር አካዳሚ ምሩቅ ናቸው። በማሊ በሚገኘው ኮውሊኮሮ ኮሌጅም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከፓሪስ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ከጀርመኑም ፌደራል አርሚ ዩኒቨርስቲም በሲቪል ምህንድስና የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።