ብራዚል፡ተደፍራ ያረገዘች ታዳጊ ፅንስ እንዳታቋርጥ በሚል መረጃዋ መውጣቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባት የአስር አመት ታዳጊ ዝርዝር መረጃ በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ ድረገፆች ላይ መውጣቱ በርካታ ብራዚላውያንን አስቆጥቷል።
የልጅቷ ስምና ዝርዝር መረጃ የወጣው ፅንስ ማቋረጥን በሚቃወሙ ቡድኖች እንደሆነም ተገልጿል።
ታዳጊዋ በመደፈሯ ያረገዘች ሲሆን ፅንሱንም ለማቋረጥ ከሰሞኑ ቀጠሮ ተይዞላት ነበር።
ፅንሱን ማቋረጥ የለባትም የሚሉት እነዚህ ቡድኖች መረጃዋን ከማውጣት በተጨማሪም ሆስፒታሉም ደጃፍ ላይ ለተቃውሞ ተሰባስበው ነበር።
ታዳጊዋን የደፈራት ግለሰብ ከሰሞኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
የታዳጊዋ መረጃ መውጣት በብራዚላውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ማቀጣጠሉን ተከትሎ ጉግል፣ ፌስቡክና ትዊተር የታዳጊዋን የግል መረጃ ከገፆቻቸው እንዲያጠፉ አንድ ዳኛም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ዳኛ ሳሙኤል ሚራንዳ ጎንካልቭስ ኩባንያዎቹ መረጃውን ለማጥፋት 24 ሰዓታት የሰጧቸው ሲሆን፤ ይህንን ተግባራዊ የማያደርጉ ከሆነ በቀን 9 ሺህ ዶላር እንዲቀጡም ወስነዋል።
ፅንስ ማቋረጥ ላይ ጠበቅ ያለ ህግ ያላት ብራዚል በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን ፍቃድ አለው።
ለተደፈሩ፣ የእናቲቷ ህይወት አደጋ ውስጥ በሚገባበት ወቅት እንዲሁም ፅንሱ መወለድ የማይችልበት ህመም ካለው ፅንስ ማቋረጥ ይፈቀዳል።
ታዳጊዋ ፅንሱን የማቋረጥ ህጋዊ ድጋፍ ቢኖራትም ይህንን የሚቃወሙ ቡድኖች በሆስፒታሉ ደጃፍ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የሆስፒታሉን ሰራተኞችም "ነፍሰ ገዳዮች" እያሉም ሲጮሁባቸው የነበረ ሲሆን ወደ ሆስፒታሉ ውስጥ ለመግባት የሞከሩም እንዳሉ ተነግሯል።
የፀጥታ ኃይሎችም ጣልቃ በመግባት በትነዋቸዋል ተብሏል።
የፅንስ ማቋረጥን እንደ ምርጫ የሚያዩት ደጋፊዎች ታዳጊዋን በመኪና ደብቀው ያመጧት ሲሆን በሆስፒታሉም በኋላ በር እንዲሁ ደብቀው አስገብተዋታል።
የቢቢሲ ደቡብ አሜሪካ ዘጋቢ ካቲ ዋትሰን እንደምትናገረው የታዳጊዋን መረጃ ይፋ ያደረገችው በፅንፈኝነቷ የምትታወቀው ሳራ ጂሮሚኒ የምትባል ግለሰብ መሆኗን ነው።
ሳራ የታዳጊዋን መረጃ ይፋ በማድረጓ ክስ ይጠብቃት እንደሆነ እስካሁን ያልተገለፀ ሲሆን የህግ ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭትን በማነሳሳት ልትከሰስ እንደምትችል ጠቁመዋል።
ሳራ ጂሮሚኒ "ኦስ 300 ዱ ብራሲል" የተባለ የቀኝ ክንፍ አክራሪ እንቅስቃሴ መሪ ስትሆን የፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮም ቀንደኛ ደጋፊ ናት ተብሏል።
በሰኔ ወር ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት አካባቢ "ፀረ-ዲሞክራሲያዊ" ሰልፍ አስተባብራለች በሚልም ለአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር።












