ፊልም፡ ከኮሮና በኋላ ኔትፍሊክስ ላይ የተከሰቱ 5 ነጥቦች

ቻርሊዝ ቴሮን የምትሰራበት "ዘ ኦልድ ጋርድ" በሩብ ዓመቱ ምርጡ ፕሮዳክሽን ተብሏል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አገራት በራቸውን ሲዘጉ በበይነመረብ ላይ መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች ገበያቸው ተመነደገ፡፡ የበይነመረብ አቡጀዲ ዘርግቶ ፊልም የሚያስኮመኩመው ኔትፍሊክስም ደንበኞቹ በዙለት፡፡

ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ኔትፍሊክስ ምን ሆነ? ምን አጋጠመው? እየተነሳ ነው እየወደቀ? 5 ጉዳዮችን ብቻ ተመልክተናል፡፡

1፡የኔትፍሊክስ ደንበኞች አሁንም እየጨመሩ ነው።

ወረርሽኙ ገበያቸውን ካደራላቸው ዘርፎች መሀል ፊልሞችን በበይነ መረብ በማቅረብ የሚታወቀው ኔትፍሊክስ ይገኝበታል፡፡

ድርጅቱ በ13 ዓመታት ታሪኩ አይቶት የማያውቀውን ገበያ ነው ማጋበስ የቻለው፡፡ ኔትፍሊክስ ከኮቪድ በኋላ ብቻ 2.2 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን አግኝቷል፡፡ እነዚህ ታዲያ ከሴፕቴምበር 30 በኋላ ብቻ የተመዘገቡ ደንበኞች ናቸው፡፡

የደንበኞች ቁጥር መጨመሩ እንዳለ ሆኖ ግን አዳዲስ ደንበኞች የሚመጡበት ፍጥነቱ ከዚያ በኋላ እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡ ኔትፍሊክስ ያያዝነው የፈረንጆች ዓመት ከመገባደዱ በፊት ብቻ 34 ሚሊዮን አዳዲስ ተመዝጋቢዎች እንደሚኖሩት ተስፋ ያደርጋል፡፡

በጠቅላላው ደግሞ የዓለም አቀፍ ደንበኞቹ ብዛት እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ 200 ሚሊዮን ለማድረስ እየሰራ ነው፡፡

2፡ ብዙ ሰው የተመለከተው ፊልም የቱ ነው?

ኔትፍሊክስ ባለፉት 3 ወራት ከፍተኛ ተመልካች ያገኘልኝ ፊልም ‹‹ዘ ኦልድ ጋርድ›› ነው ብሏል፡፡ 78 ሚሊዮን ደንበኞቼና ቤተሰባቸው ይህንን ፊልም በወጣ በ4 ሳምንታት ውስጥ ብቻ ተመልክተውልኛል ይላል፡፡

ቻርሊስ ቴሮን የምትተውንበት ይህ ትእይንተ-ብዙ (Action) ዘውግ ያለው ፊልም ነው፡፡ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ ኢኖላ ሆልምስ (Enola Holmes) 76 ሚሊዮን ደንበኞች፣ ፕሮጀክት ፓወርን (Project Power) 75 ሚሊዮን ደንበኞች እና ዘ ኪሲንግ ቡዝ-2 (The Kissing Booth 2) 66 ሚሊዮን ደንበኞች ተመልክተዋቸዋል፡፡

ይህ አሐዝ ፊልሞቹ በወጡ በ4 ሳምንታት ውስጥ ያለውን እውነታ ብቻ የሚያመላክት ነው፡፡ ኔትፍሊክስ አንድ ሰው ፊልሙን ተመልክቶታል ብሎ የሚመዘገብው ደንበኛው ከ2 ደቂቃ በላይ ከቆየ ነው፡፡

ዘ ጉድ ፕሌስ የተሰኘው አስቂኝ ተከታታይ ድራማ በኔትፍሊክስ ከተወደዱት መካከል ነው

የፎቶው ባለመብት, Netflix

3 ከአሜሪካ ውጭ ያለው ገበያ ወሳኝ ነው?

የዓለማቀፍ ደንበኞች ቁጥር ለኩባንያው እጅግ ወሳኝ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ በአሜሪካ የሚገኙ ደንበኞች ቁጥር ከዓለማቀፍ ደንበኞች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ሆኗል፡፡

ዋነኛዎቹ የኔትፍሊክስ ደንበኞች እየተመዘገቡ ያሉት በኢሲያና ፓስፊክ አካባቢ ነው፡፡ ጥሩ የኢንተርኔት ፍጥነት ያለባቸው ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ደንበኞች ኔትፍሊክስን ይመርጣሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ በተጠቃሚ ደረጃ ገቢ ሲሰላ ለኩባንያው የተሻለ ሆኖ የተገኘው በአሜሪካ ከሚገኙ ደንበኞቹ የሚሰበሰው ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ሲያማትር ኔትፍሊክስ የአሜሪካ ደንበኞቹን ቸል ማለት እንደማይገባው ማሳያ ነው፡፡

በአሜሪካ ደግሞ ዲዝኒ እና ኤችቢኦ (HBO) ገበያውን እየተቀራመቱት ነው፡፡

4፡ ቀጣዩ ፈተናስ?

የፊልምና የቴሌቪዥን ትእይንት አምራች ኩባንያዎች በኮቪድ ምክንያት ተዘግተዋል፡፡ አሁን ኔትፍሊክስም ሆነ ሌሎቹ ተወዳዳሪዎች እነ ዲዝኒ፣ ደንበኞቻቸው እንዳይርቋቸው አዳዲስ ሥራዎችን ይዘው መምጣት ይገባቸዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ ይቸገራሉ ይላሉ የቢዝነስ ተንታኞች፡፡ ኔትፍሊክ ግን 2021 ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አዳዲስ ሥራዎችን ይዤ የምቀርብበት ነው የሚሆነው አታስቡ ይላል፡፡

5፡ ትርፍ ምን ያህል ነው?

በበጀት ዓመቱ የመጨረሻ ሩብ ዓመት ብቻ ኔትፍሊክስ አገኘሁ ያለው ትርፍ 790 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የዓመት ትርፉ 6.4 ቢሊዮን ይደርሳል፡፡

ኩባንያው እንደሚለው አዳዲስ ሥራዎችን መግዛት ወጪ በመቀነሱ፣ ትእይንቶችም ባለመኖራቸው ያሉትን ለደንበኞቹ በማቅረብ የትርፍ ህዳጉን ማሳደግ ችሏል፡፡