ፊልም ፡ የአንድ ቅምጥል ቤተሰብን ኑሮ የሚያሳየው ተወዳጁ የቴሌቪዥን ትዕይንት ተቋረጠ

ተዋንያኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ገሀዳዊ የቴሌቪዥን ትዕይንት ነው። ላለፉት 14 ዓመታት ተላልፏል። ሚሊዮኖች ይመለከቱት ነበር።

ይህ ትዕይንት በአንድ የናጠጠ ሃብታም ቤተሰብ ኑሮ ላይ የተመሰረተ እውናዊ ትዕይንት ነበር።በአጭሩ ትዕይንቱ የቅምጥል ሀብታም ቤተሰብን ሕይወት ቁጭ ብሎ መመልከት ነው።

ኪም ካርዳሺያን ዌስት የቴሌቪዥን ትዕይንቱ መቋረጡን ይፋ አድርጋለች። በትዊተር ሰሌዳዋ ላይ በጻፈችው የስንብት ጽሑፍ "ከባድ ውሳኔ ነበር። ልብ የሚሰብር ዜና ነው። ከካርዳሺያን ቤተሰብ ጋር ይህን ያህል ስለቆያችሁ አመሰግናለሁ፤ ደህና ሁኑልን" ብላለች።

ትዕይንቱ በ14 ዓመታት ቆይታው ኪምና ቤተሰቧን በከፍተኛ ሁኔታ አበልጽጓል። ዓለም እንዲያውቃቸውም አድርጓል።

እርግጥ ነው ድሮም ብልጹግ ነበሩ። የመጨረሻው የትዕይንቱ ክፍል 2021 የመጀመሪያው ወር ላይ ይታያል ተብሏል።

ኪም በስንብት መልዕክቷ ትዕይንቱን በገንዘብ የደገፉትን ሁሉ አመስግናለች። "ላለፉት 14 ዓመታት ከእኛ ጋር ስለሆናችሁ እንዴት ማመስገን እንዳለብኝ አላውቅም" ብላለች።

ይህ ትዕይንት በ2007 ሲጀመር አብዛኛዎቹ የካርዳሺያን ቤተሰብ አባላት እምብዛም የሚታወቁ አልነበሩም። ኪም ብቻ ፓሪስ ሂልተን በነበራት የቲቪ ትዕይንት በተወሰኑ መልኩ ትታይ ነበር። ከዚያ ውጭ የኪም አባት እውቅ ነበር።

የኪም አባት ሮበርት ዓለምን ባነጋገረው የኦ ጄ ሲምሰን የፍርድ ሂደት ላይ ጠበቃ በመሆን ይታወቃሉ። በኋላ ጠበቃ ሮበርት ካርዳሺያን በ2003 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የመጀመርያ አካባቢ የነበሩት ትዕይንቶች የኪምና የእህቶቿ ከርተኒ እና ክሎ እና የእነሱ የወንድ ወዳጆቻቸውን ሕይወት ያካተተ ነበር። የከርተኒ የቀድሞ ወንድ ጓደኛ ስኮት ዲሲክ የኪም የቀድሞ ባሏ ክሪስ ሀምፍሪስ እና የክሎ የቀድሞ ባሏ ላማር ኦዶም የትዕይንቱ አካላት ነበሩ።

ምንም እንኳ ይህ ትዕይነት እዚህ ግባ የሚባል የቁም ነገር ይዘት ወይም ሌላ ይህ ነው የሚባል ጭብጥ ባይኖረውም እጅግ ተወዳጅ ሆኖ ቆይቷል።ተቺዎች "ዝነኛ ሰዎችን ይበልጥ ዝነኛ ከማድረግ ያለፈ ትርጉም የሌለው ከንቱ የቴሌቪዥን ትዕይንት ነበር" ይሉታል።

ዓለም ግን እንቅልፉን አጥቶ ሲመለከተው ኖሯል።ኪም አሁን 39 ዓመቷ ሲሆን በዓለም ዝነኛ ሴቶች ተርታ ትሰለፋለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮችንም አፍርታለች። የሙዚቃ አቀንቃኙን ካንዬ ዌስትን አግብታ ትኖራለች። ካንዬን ከስድስት ዓመታት በፊት ያገባችው ሲሆን አሁን በጋራ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።

በጋራ ሀብታቸው 1 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ካንዬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠነኛ የአእምሮ ጤና መቃወስ እንደገጠመው ይነገራል። ኬንዳል እና ኬሊ ጄነር ትዕይንቱ ሲጀመር ሕጻናት የነበሩ ሲሆን ምንም ሳይሰሩ አሁን በዓለም እውቅ ልጃገረዶች ተርታ ተመድበዋል። እድሜያቸውም 23 እና 24 ደርሷል።

ኬሊ ጀነርን ለምሳሌ በ2019 ፎርብሰስ መጽሔት ትንሽዋ ቢሊየነር ሲል ሰይሟታል።የኢ ኢንተርቴይመንት ቃል አቀባይ ለሲኤንኤን ቴሌቪዥን በሰጠው አስተያየት ውሳኔያቸው ልብ የሚሰብር ቢሆንም፤ "የቤተሰቡን የመጨረሻ ውሳኔ ማክበር ይኖርብናል፤ ከእኛ ካሜራ ውጪ ሕይወታቸውን መኖር ምርጫቸው ከሆነ ያንን እናከብራለን" ብሏል።