ናይጄሪያ፡ በተቀደሰች ሥፍራ የወሲብ ፊልም የሠራው ግለሰብ ታሠረ

የኦሹን የተቀደሰ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡባዊ ናይጄሪያ በአንድ ቅድስት በተባለች ሥፍራ የወሲብ ፊልም የቀረፀው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አሰታወቀ።

ኦሹን ኦሶግቦ የተባለችው ቅድስት ጫካ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቅርስ ተብላ የተመዘገበች ሥፍራ ናት።

ኦሹን የዮሩባ ጎሳ አማልክት እንደሆነች ይታመናል።

ፖሊስ እንዳለው ቲበላክ ሆክ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ቶቢሎባ ጆላሾ ጫካው ውስጥ የወሲብ ፊልም በመቅረፁ ነው ለእሥር የተዳረገው።

ግለሰቡም ሆነ ጠበቃው እስካሁን ስለጉዳዩ አስተያየት አልሰጡም።

ኦሹን ኦሶግባ ጫካ ኮሶግባ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘ በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅድስት ተደርጋ የምትቆጠር ሥፍራ ናት።

በርካታ ተከታዮች ያሉት የወሲብ ፊልም ሠሪው ጆላሾ በማሕበራዊ ሚድያ ገፆቹ ላይ የለቀቀው ቅንጭብ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ኦሹን ለተሰኘችው አማልክት እንደሚሰግዱ ሰዎች ለብሶ ይታያል።

ምንም እንኳ ወደ ጫካው ለመግባት ቀላል ቢሆንም ሰውዬው ምስሉን በየት በኩል ገብቶ መቼ እንደቀረፀው እስካሁን አልታወቀም።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ኦፓሎላ የሚሲ፤ ፊልም ሠሪው ፈፀመ በተባለው ወንጀል ላይ ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰውዬው የአካባቢውን ሰላም አደጋ ላይ በመጣል ሊከሰስ ይችላልም ብለዋል።

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አምላኪዎች ከናይረጄሪያና ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ጫካው በመምጣት ለወንዝ አምላኳ ኦሹን ስጦታዎች ያበረክታሉ።

ከኦሹን አምላኪዎች አንዷ የሆነችው የሚ ኤሌቢቦን ሰውዬው ጫካው ውስጥ የወሲብ ፊልም በመቅረፁ የሥፍራዋን ቅድስትነት አርክሷል ትላለች።

ከፖሊስ ምርመራ በኋላ ጥንታዊ አምላኪዎች ሰውዬው ይገባዋል የሚሉትን ቅጣት እንደሚጥሉበት የሚ ለቢቢሲ ትናገራለች።

በአውሮፓውያኑ 2003 ዓ.ም. በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆና የተመዘገበችው የኦሹን ኦሶግቦ ቅድስት የመቃብር ሥፍራ በምዕራባዊ ናይጄሪያ ጥንታዊ ከሚባሉ ጫካዎች አንዱ ነው።

በዮሩባ ጎሳ አባላት እምነት መሠረት ኦሹን ሳንጎ ከተሰኘው አምላክ ሚስቶች መካከል አንዷ ናት።

አማኞች በየዓመቱ ወደ ሥፍራው እየመጡ መስዋዕት የሚያቀርቡላት ይህ እምነት 600 ዓመት የዘለቅ እንደሆነ ይነገራል።

ለሁለት ሳምንታት የሚቆየው ይህ ክብረ በዓል በዮሩባ ሰዎች ዘንድ ትልቁ በዓል ነው።