አውስትራሊያ፡ የተጠርጣሪውን ጭንቅላት ረግጦ መሬት ላይ ያጣበቀው ፖሊስ ታገደ

ፖሊሶች ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በሚያውሉበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, JAKE EDWARDS

በአውስትራሊያ ፖሊስ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር በሚያውልበት ወቅት በመኪና ገጭቶ ጭንቅላቱን መርገጡን ተከትሎ ከስራ ታግዷል።

ክስተቱ የደረሰው በሜልቦርን ከተማ ዕሁድ እለት ነበር።

የ32 አመቱ ተጠርጣሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ሲያውሉት ባደረሱበትም አደጋ በፅኑ ህሙማን ክፍል በሞትና በህይወት መካከል ውስጥ ነው ያለው ተብሏል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር በሚውልበት ወቅት ተቀረፀ የተባለ ቪዲዮ መውጣቱንም ተከትሎ ቤተሰቡ ነፃ ምርመራ እንዲከፈት ጥሪ አድርጓል።

የቪክቶሪያ ፖሊስም ውስጣዊ ምርመራ ጀምሬያለሁ ብሏል።

በባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የሜልቦርን ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በወጣው መመሪያ ምክንያት ጥብቅ የእንቅስቃሴ እግድ ላይ ናት።

ከጤና ጋር በተያያዘ ለዚህ ስጋት የሚሆኑና መመሪያዎችን ጥሰው የሚገኙ አውስትራሊያውያኖችንም በቁጥጥር ስር እንዲያውሉና እንዲቀጡ ፖሊሶች ከፍተኛ ኃይል ተሰጥቷቸዋል።

የእሁዱ ሁኔታ ግን ከኮሮናቫይረስ መመሪያ ጋር የተያያዘ አይደለም ተብሏል።

ግለሰቡ ከፖሊስ ጋር ያለው ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት ወደ አዕምሮ ጤና ሆስፒታል ለህክምና ሄዶ ነበር።

የሆስፒታሉ ሰራተኞችም ናቸው ለፖሊስ የደወሉት።

ሁኔታውን ሲከታተል የነበረ ግለሰብ የቀረፀው ቪዲዮ እንደሚያሳየው አንደኛው ፖሊስ ጭንቅላቱን በእርግጫ ሲመታውና መሬት ላይ ሲያጣብቁት ይታያል።

የቪክቶሪያ ፖሊስ ግለሰቡ ነውጠኛ ባህርይ እያሳየና አንደኛው ፖሊስም ላይ ጥቃት አድርሷል ብሏል።

በሰቨን ኒውስ የቴሌቪዥን ጣቢያ የታየው ይህ ቪዲዮ ላይ ግለሰቡ መሃል ጎዳና ላይ ሲራመድና እጁን ወደ ፖሊስ መኪናው አቅጣጫ ሲያውለበልብ ይታያል።

ከዚያም ዘወር ብሎ ቀስ ብሎ ሲራመድ የሚታይ ሲሆን የፖሊስ መኪናውም ይገጨዋል።

ከደቂቃዎች በኋላ የተቀረፀ ሌላ ቪዲዮም እንደሚያሳየው አንደኛው ፖሊስ ጭንቅላቱን ሲረግጠውና ከመሬት ጋር ሲያጣብቀው ይታያል።

ከዚያም ይህንን ፖሊስ ጨምሮ አምስት ሌሎች ፖሊሶች ከመሬት ጋር አጣብቀውት ይታያል።

ጥቃት የደረሰበት ግለሰብ አባት ፖሊስ ያልተገባ ኃይል ተጠቅሟል ብሏል።

"አሜሪካ ወይም ቤይሩት የተቀረፀ ቪዲዮ የማይ ነው የመሰለኝ" በማለትም ለሄራልድ ሰን ጋዜጣ ተናግረዋል።

"ፖሊስ ከህግ በላይ አይደለም። ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል። እየረገጡትና እየደበደቡት ነበር፤ እሱም በምላሹ እንኳን እየታገለ አልነበረም። ያልተገባ ተግባር ነው" ብለዋል።

ጠበቃው ጄረሚ ኪንግ ለኤቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት ደንበኛቸው ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈፀመና በቁጥጥር ስር በዋለበትም ወቅት አእምሮው ባልተረጋጋበት ወቅት ነው ብለዋል።

"ግለሰቡ ካለበት ሁኔታ አንፃር ፖሊስ ሊንከባከበው በሚያስፈልግበት ወቅት፣ በተለየ መንገድ ሊያየው ይገባ ነበር" ብለዋል።

ፖሊስ በበኩል ግለሰቡ ሲረብሽ እንደነበርና በቁጥጥር ስር አልውልም ብሎ በማስቸገርም የፖሊስ መኪና አበላሽቷል ብሏል።

ሆኖም ክስተቱ አሳሳቢ ነገሮች ስላሉበት ምርመራ እንደሚከፈትም ተገልጿል።