ሴቶችን በማታለል ልቅ የወሲብ ፊልም ያሠራጨው ድረ-ገፅ ባለቤት በኤፍቢአይ እየተፈለገ ነው

አልጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መሠረቱን አሜሪካ ያደረገው 'ገርልስዱፖርን' [GirlsDoPorn] የተሰኘው የልቅ ወሲብ ድረ-ገፅ ባለቤት በአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ቢሮ እየተፈለገ ነው።

የድረ-ገጹ ባለቤት 22 ሴቶችን አታሎ ልቅ የወሲብ ተንቀሳቃሽ ምስላቸው በወሲብ ድረ-ገጾች ላይ በማስራጨቱ ለ22ቱ ሴቶች ካሳ እንዲከፍላቸው ፍርድ ቤት በይኖበት ነበር።

የድረ-ገፁ ባለቤት ማይክል ፕራት ድረ-ገጹን ካጠፋ በኋላ እንዲከፍል የተበየነበትን ካሳ ሳይከፍል ተሰውሯል።

ማይክል ፕራት በአጠቃላይ 12.8 ሚሊየን ዶላር (384 ሚሊዮን ብር በላይ) በካሳ መልክ እንዲከፍል ነበር የተወሰነበት።

'ገርልስዱፖርን' የተባለው ድረ-ገጽ መሥራት ካቆመ አንድ ሳምንት እንዳለፈው ተነግሯል።

ከሳምንታት በፊት የሳንዲያጎ ዳኛ ድረ-ገጹ ሴቶቹ ምስላቸው በድረ-ገጾች ላይ እንደማይጫኑ፤ ትክክለኛ ስማቸውንም እንደማይጠቀም እንዲሁም የሚያውቋቸው ሰዎችም ምስሎቹን እንማይመለከቱ ቃል ቢገባላቸውም ምስላቸው በሌሎች ድረ-ገጾች ጨምር መሰራጨቱን አረጋግጫለሁ ብለዋል።

በዚህም ሴቶቹ ላይ የተለያየ አይነት ጥቃት ከመድረሱም ባሻገር፤ ለሞራል እና ለሥነ ልቦና ችግር ተዳርገዋል። ከሥራቸው የተሰናበቱ እና ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ጭምር እንዳሉ፤ እንዲሁም ከቤተሰብና ጓደኞቻቸው ጋር መልካም ግንኙነታቸው እንዳጡ የሳንዲያጎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ኬቨን ኢንራይት ተናግረዋል።

የድረ-ገፁ ባለቤት ማይክል ፕራት ምናልባትም ወደ ኒውዚላንድ ሳይሸሽ እንማይቀር ተነግሯል።